ቱርካዊቷ በሳምንት አንዴ እንኳን ሰውነቱን አይታጠብም ያለችውን ባሏን ፍቺ ጠይቃለች
ተከሳሹ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ልብሱን አይቀይርም የሚል ክስም ከሚስቱ ቀርቦበታል
ክሱን የተመለከተው ፍርድቤትም የፍቺ ጥያቄውን ተቀብሎ፥ ተከሳሹ 16 ሺህ 500 ዶላር ካሳ እንዲከፍል ወስኗል
በቱርክ የግል ንጽህናውን አይጠብቅም የተባለው ባል በሚስቱ ክስ ተመስርቶበታል።
የስሟ የመጀመሪያ ፊደሎች “ኤ ዋይ” መሆናቸው የተነገረላት ሚስት ያቀረበችው ክስ በአንካራ በሚገኘው 19ኛ የቤተሰብ ችሎት እየታየ መሆኑን የቱርክ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
“ባሌ በሰባት ወይም አስር ቀናት ውስጥ አንዴ ብቻ ነው ሰውነቱን የሚታጠበው፤ ላብ ላብ ይሸታል፤ አንድ ልብስን ከአምስት ቀናት በላይ ሳይቀይር ይለብሳል፤ ጥርሱንም በሳምንት አንዴ ወይ ሁለቴ ነው የሚቦርሸው” ብላለች ከሳሽ ሚስት።
በዚህም ጤናዋም ሆነ ትዳራቸው አደጋ ላይ መውደቁን በመጥቀስ ፍቺ መጠየቋ ተሰምቷል።
ምስክር ሆነው የቀረቡት የጋራ ወዳጆቻቸውና የስራ ባልደረቦቹም ግለሰቡ ንጽህናውን እንደማይጠብቅ በአንድ ቃል መመስከራቸው ነው የተነገረው።
ግለሰቡ ንጽህናውን አለመጠበቁ በስራ ቦታም ቅሬታ መፍጠሩን ባልደረቦቹ ለፍርድቤት አስረድተዋል።
ክሱን የተመለከተው ችሎትም የፍቺ ጥያቄ ተቀብሎ የግል ንጽህናውን ባለመጠበቅ ትዳሩ የፈረሰበት ባል 500 ሺህ የቱርክ ሊራ ወይም 16 ሺህ 500 ዶላር ካሳ እንዲከፍል ወስኗል።
የከሳሿ ጠበቃ ሰነም ዪልማዘል “የትዳር አጋሮች በጋራ ለሚመሩት ህይወት ሃላፊነት አለባቸው፤ የግል ንጽህናን አለመጠበቅ ለፍቺ ሊዳርግ እንደሚችል ማወቅ ተገቢ ነው” ሲሉ ለቱርኩ ጋዜጣ ሳባህ ተናግረዋል።
ሰውነትን ያለመታጠብና ንጽህናን ያለመጠበቅ ጉዳይ በተደጋጋሚ ለትዳር መፍረስ ምክንያት ሲሆን ይታያል።