በሰርጓ ዕለት ሙሽራዋ የጠፋባት ሙሽሪት የባሏን አባት አገባች
ሰርጉን ለማድመቅ በስፍራው ተሰብስበው የነበሩ የሁለቱም ቤተሰቦች በመጨረሻም የተሻለውን ውሳኔ ወስነዋል ተብሏል
በሰርጉ ዕለት ደብዛው የጠፋው ሙሽራ እስካሁን ለምን እንደጠፋ አልታወቀም
በሰርጓ ዕለት ሙሽራዋ የጠፋባት ሙሽሪት የባሏን አባት አገባች፡፡
ክስተቱ የተፈጠረው ባሳለፍነው ሳምንት ነሀሴ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በእስያዊቷ ኢንዶኔዢያ ሲሆን ጉዳዩ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡
ጥንዶቹ ለረጅም ጊዜ በፍቅር ቆይተዋል የተባለ ሲሆን ለመጋባት ከወሰኑ በኋላ የተለያዩ ዝግጅቶችን አድርገው ሁሉንም ነገር ጥንቅቅ አድርገው አሟልተው ቤተሰቦቻቸውን እና ጓደኞቻቸውን ጠርተዋል፡፡
ይሁንና ጋብቻው በሚፈጸምበት ዕለት ሙሽራው ቢጠበቅ ቢጠበቅ መጥፋቱ ሙሽሪትን አሳዝኖ ነበር ተብሏል፡፡
ጋብቻውን ለማድመቅ በሰርጉ ላይ የተገኙት የተጋቢ ቤተሰቦችም አብረው ተጨንቀው ነበር የተባለ ሲሆን በመጨረሻም የሙሽራው ቤተሰቦች ተመካክረው የተሻለውን ውሳኔ እንደወሰኑ ተገልጿል፡፡
ሰርጉ በአሳዛኝ መልኩ እንዳይጠናቀቅ፣ ለሰርጉ የወጣው ወጪም እንዳይባክን ሙሽሪትንም ከከፋ ጉዳት ለመጠበቅ በሚል የሙሽራው አባት ከልጃቸው ፍቅረኛ ጋር ለመጋባት ሀሳብ ያቀርባሉ፡፡
ሙሽሪት እና ቤተሰቦቿም በቀረበላቸው ሀሳብ ተስማምተው ጋብቻው ተፈጽሟል የተባለ ሲሆን ጉዳዩ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡
የኡጋንዳ ፖሊስ ሙሽሪት በሰርግ ላይ ሳለች በቁጥጥር ስር አውለዋል ባላቸው አባላቱ ላይ ክስ መሰረተ
ጥንዶቹ ለዚህ ጋብቻው 25 ሚሊዮን የኢንዶኔዚያ ሩፒያህ ወይም 1 ሺህ 700 ዶላር ወጪ አውጥተዋል ተብሏል፡፡
ጋብቻው ሲፈጸም የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ የትስስር ገጾች መለቀቁን ተከትሎ የሀገሬው ዜጎች አስተያየታቸውን በድጋፍ እና በትችት መልክ በማጋራት ላይ ናቸው፡፡
ብዙዎቹ ደብዛው የጠፋውን ሙሽራ በመተቸት አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ አንዳንዶቹ የአባትየውን ውሳኔ ሲያደንቁ ቀሪዎቹ ደግሞ በጋብቻው ላይ ምጸታዊ አስተያየቶችን ሰጥተዋል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
እንዲሁም ሙሽሪት እና ቤተሰቦቿ ከባሏ ቤተሰቦች የቀረበላቸውን ሀሳብ መቀበል አልነበረባቸውም የሚሉ አስተያየቶች በማህበራዊ ትስስር ገጾች በመሰራጨት ላይ ናቸው፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ጋብቻውን በሚፈጽምበት ዕለት የጠፋው ሙሽራ እስካሁን ለምን እንደጠፋ እና አሁን የት እንዳለ አይታወቅም ተብሏል፡፡