ርዕደ መሬት የኢንዶኔዥያ ሙስሊሞችን ለሰላት ወደ ሜዳ አስወጥቷቸዋል
በሀገሪቱ ጃቫ ግዛት የደረሰው ርዕደ መሬት መስጂዶችን በማፈራረሱ ነው በአውሮ ጎዳናዎች እና በእጅ ኳስ ሜዳዎች ለሰላት መሰባሰብ የጀመሩት
በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 310 ደርሷል
በኢንዶኔዥያ የጃቫ ግዛት ሙስሊሞች ትናንት ለሰላት ስግደት ወደ መስጂዶች አላመሩም።
ርዕደ መሬት ያስከተለው አደጋ ሜዳ ላይ ለመስገድ አስገድዷቸዋል።ከመዲናዋ ጃካርታ 75 ኪሎሜትር ርቃ በምትገኘው ሲንጁር ከተማ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 6 ሆኖ የተመዘገበ ርዕደ መሬት ተከስቷል።
አደጋው በከተማዋ የሚገኘውን መስጂድ በማፈራረሱ ሙስሊሞች የሰላት ስግደታቸውን በእጅ ኳስ ሜዳ አድርገዋል።
የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው አሁንም ዳግም ሊከሰት ስለሚችል ሜዳውን መርጠናል ብለዋል ሙሀመድ የተባሉ የ52 አመት ጎልማሳ።
በአደጋው ቤቱ የፈረሰበት አሴፕ ሂዳያት በመስጂድ ውስጥም ባይሆን አምላክን ለማመስገን በመገናኘታችን ደስ ብሎኛል የሚል አስተያየቱን ለሬውተርስ ሰጥቷል።
በጊዜያዊ መጠለያዎች የሚገኙት በሽዎች የሚቆጠሩ መሆናቸውን ጠቅሰው በችግር ውስጥም ሆነው ፈጣሪን ማመሰገን መስገድ ወሳኝ መሆኑን ነው ያነሱት።
ሙሀመድ ጃምሁር በመሩት ሰላት በመቶዎች የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች ተገኝተዋል።
በሌሎች የጃቫ ግዛት ከተሞችም በአውራ መንገዶች እና ሜዳማ አካባቢዎች መሰባሰብ ተመራጭ እየሆነ ነው።
በኢንዶኔዥያ የደረሰው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ በተለይ ተራራማ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
ነዋሪዎችም ከ310 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው አደጋን በመፍራት ሜዳማ አካባቢዎች ላይ ውሏቸውን እያደረጉ ነው። በድንኳን የሚገኙ በሺዎቾ የሚቆጠሩ ሰዎች የምግብ፣ ውሃ፣ መድሃኒትና ሌሎች ድጋፎች እየተደረገላቸው ይገኛል።