ሴቶችን ስለማከብር ከጊዜያዊ ግንኙነት ይልቅ በትዳር መተሳሰሩን መርጫለሁ ያሉት ሩዝ አምራች አርሶ አደር በ88ም የሚቆሙ አይመስልም
የ61 አመቱ ኢንዶኔዥያዊ አርሶ አደር አዲስ ትዳር በመመስረት ተጠምደዋል።
ለ88ኛ ጊዜ ለማግባት መሰናዳታቸውን ማሳወቃቸውን ተከትሎም በአለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ሆነዋል።
በምዕራብ ጃባ ግዛት ሩዝ በማምረት የሚተዳደሩትና ካን በሚል ስማቸው በአጭሩ የተጠቀሰው አዛውንት፥ በሀገሪቱ ለሚሰራ አንድ ዩቲዩበር ታሪካቸውን ካጋሩ በኋላ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስበዋል።
ዝናቸው የናኘው ካን ቃለመጠየቅ መስጠትን ባይፈልጉም የሚኖሩበት መንደር ድረስ ደጋግመው ለዘለቁ ጋዜጠኞች ግን አልጨከኑም።አዛውንቱ ካን በ14 አመታቸው በሁለት አመት የምትበልጣቸውን ታዳጊ በማግባት አሀዱ አሉ።
ለሁለት አመት የዘለቀው የልጆች ትዳር የያኔውን ታዳጊ አዲስ ሚስት አጭቶ ከማግባት አላገደውም፤ አዲስ ትዳር መመስረት ትንሽ ቆይቶ መፍታት በፍጥነት ሌላ ለማግባት መዘጋጀትም የህይወቱ ዋነኛ መንገድ ሆ ይላል ዘገባው።
ለምን የፈቀድካትን ሴት ሁሉ ታገባለህ ተብለው የተጠየቁት አዛውንቱ ካን ሴቶችን ስለማከብር ለስሜታቸው እጨነቃለሁ፥ ከጊዜያዊ ግንኙነት ይልቅ በትዳር መተሳሰሩንም እመርጣለሁ ብለዋል።
ከሞራል ውጭ የሆኑ ተግባራትን ከመፈፀም ማግባትን እመርጣረለሁ የሚሉት ኢንዶኒዥያዊ፥ ረጅሙ የትዳር ቆይታቸው 14 አመት ነው።
አብዛኞቹ ሚስቶቻቸው ግን ከአንድ ወር እስከ አንድ ሳምንት የቆዩ ናቸው።
ካን 87 ጊዜ ትዳር ይፈፅሙ እንጂ ከ87 ሴቶች ጋር አይደለም ጎጆ የቀለሱት፤ ቢከፋኝ ብመለስ እያሉ ዳግም ያገቧቸው ሴቶች በርካታ ናቸው። በአጠቃላይ 46 ሴቶችን ነው ያገቡት።አሁን ደግሞ 88ኛ ጋብቻቸውን ከ86ኛ ሚስታቸው ጋር ለማድረግ እየተዘጋጁ ነው ተብሏል።