ደቃቋ ቺፕ ማንኛውም የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያን ከኢንተርኔት ጋር ታገናኛለች ተብሏል
የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ከሳተላይት ጋር በማገናኘት መልዕክት መላክና ኢንተርኔት መጠቀም የምታስችል ቺፕ ተዋውቃለች።
ከእጅ ጥፍር የምታንሰው ቺፕ በሰከንዶች ውስጥ ስልካችን ከሳተላይት ጋር ታገናኛለች ነው የተባለው።
የአሜሪካው ሚዲያቴክ ቺፕ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መልዕክት ለመስደድ ስማርት ስልኮችን ከሳተላይት ጋር የማስተሳሰር ሚናዋን በፍጥነት ትወጣለች።
ምንም እንኳን የተላከው መልዕክት እስኪደርስ መጠበቅ ግድ ቢሆንም ሳተላይት ፍለጋ ስልክን ወደሰማይ መያዝ አይጠበቅም ብሏል ሚዲያቴክ።
የኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎችን ከሳተላይት ኔትወርክ ጋር የምታስተሳስረው ቺፕ 10 ዶላር በማይሞላ ዋጋ መቅረቧም ተገልጿል።
የአሜሪካው አፕል በአስቸጋሪ ወቅት ከሳተላይት ጋር ተገናኝው መልዕክት መላክ የሚያስችሉ ስማርት ስልኮችን ለመጀመሪያ ጊዜ ማስተዋወቁ ይታወሳል።
ቺፕ አምራቹ ኳልኮምም ከሳተላይት ጋር የሚገናኙ ስልኮችን በዚህ አመት አጋማሽ ለገበያ እንደሚያቀርብ ይፋ አድርጓል።
የአፕልም ሆነ የኳልኮም ቺፖች ለተለየ ስማርት ስልክ ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፥ ሚዲያቴክ የሰራት ቺፕ ግን ለበርካታ ስማርት ስልኮች ጥቅም መስጠት እንደሚችል ተነግሯል።
4ጂ እና 5ጂ ኔትወርክ የሚቀበሉ ማንኛውም ስልኮች ላይ መገጠም እንደሚችል ነው የሚዲያቴክ ምክትል ፕሬዝዳንት ፊንባር ሞይኒሃን የተናገሩት።
ሞቶሮላ የሚዲያቴክ ቺፕ የተገጠመለትን ስልክ በ150 ዶላር በመሸጥ ላይ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፥ ሌሎች ስማርት ስልክ አምራቾችም ንግግር መጀመራቸውን ምክትል ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።