ሦስት ልጆቿን የገደለችው ደቡብ አፍሪካዊት እናት ጥፋተኛ ተባለች
ግለሰቧ በ2021 የሁለት ዓመት መንታ ልጆቿንና የስድስት ዓመት ልጇን በመግደል ተፈረደባት
በፍርድ ቤት የአእምሮ ህመም በዋናነት መከራከሪያ ሆኖ ቀርቧል
በኒውዝላንድ ሦስት ልጆቿን የገደለችው ደቡብ አፍሪካዊት እናት ጥፋተኛ ተባለች።
የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሎረን ዲካሰን የተባለችውን የ42 ዓመት ግለሰብ በ2021 የሁለት ዓመት መንታ ልጆቿንና የስድስት ዓመት ልጇን በመግደል የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፎባታል።
አራት ሳምንት በፈጀው ክርክርና የአእምሮ ህመም በዋናነት መከራከሪያ ሆኖ በቀረበበት ሂደት፤ ፍርድ ቤት በግለሰቧ ላይ በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ሲል ብያኔ ሰጥቷል።
የግለሰቧ ጠበቃ "እናት ልጆቿን አትገድልም፤ ደንበኛየም በጤናዋ ልጆቿን አልገደለችም" በማለት የአእምሮ ጤና አክልን ተጠያቂ አድርገዋል።
ይህን መከራከሪያቸውን የደገፉ ተከሳሽ ወገን የቀረቡ የአእምሮ ጤና ባለሞያ፤ እናት በድባቴ እየተሰቃዩ የነበሩና የዓለም ምልከታቸውም ጨለምተኛ ነበር ብለዋል።
ልጆቿን መግደሏ በሞራል ትክክለኛ እንደሆነ ማመኗንም የጠቀሱት ባለሞያው፤ እርምጃው "በበቂ ምክንያት" የተደገፈ መሆኑን ግለሰቧ መቀበሏን ገልጸዋል።
ሎረን ዲካሰን ቅጣቷ ከመተላለፉ በፊት ለምርመራ ሆስፒታል ትቆያለች ሲል አናዶሉ ዘግቧል።