ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ዚምባብዌ በፕሬዝዳንት ኢብራሂም ሬሲ የሚጎበኙ ሀገራት ናቸው
የኢራኑ ፕሬዝዳንት አፍሪካን መጎብኘት ጀመሩ፡፡
ከምዕራባዊያን ጋር ግጭት ውስጥ ያለችው ኢራን ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ማጥበቅ እንደምትፈልግ አስታውቃለች፡፡
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ሬሲ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ዛሬ የጀመሩ ሲሆን ጎረቤታችን ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ዚምባብዌ ደግሞ በፕሬዝዳንቱ የሚጎበኙ ሀገራት ናቸው፡፡
ኢራን ባለፉት 11 ዓመታት ወደ አፍሪካ በከፍተኛ ባለስልጣን ደረጃ ያልመጣች ሲሆን ፕሬዝዳንት ሬሲ የመጀመሪያ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ከቴህራን ናይሮቢ ጉዞ ጀምረዋል፡፡
አፍሪካ የእድሎች አህጉር ናት የምትለው ኢራን ግንኙነቷን ለማደስ ፍላጎት እንዳላትም የሀገሪቱ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ ተናግረዋል፡፡
ኢራን ላለፉት ዓመታት በአፍሪካ ያሉ እድሎችን ችላ ስትል መቆየቷ ስህተት መሆኑን ያሳወቀች ሲሆን ቱርክ፣ ቻይና እና ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እድሉን ሲጠቀሙበት መቆየታቸውንም አስታውቃለች፡፡
ኢራን ባሳለፍነው ዓመት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ወደ አፍሪካ ልካለች የተባለ ሲሆን የኬሚካል ምርቶች፣ መድሃኒት፣ የምህንድስና እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች ደግሞ የተላኩ ምርቶች ናቸው፡፡
የኢራን ፕሬዝዳንት ከአንድ ወር በፊት ወደ ደቡብ አሜሪካ አምርተው ከቬንዙዌላ፣ ኩባ ኒካራጉዋ መሪዎች ጋር የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብር ስምምነት ተፈራርመው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡