በርካታ የዓለም ሀገራት የገና በዓልን ዛሬ ሲያከብሩ፤ ኢትዮጵያና ሩሲያን ጨምሮ 14 ሀገራት ደግሞ ታህሳስ 29 ያከብራሉ
የእየሱስ ክርስቶስን ልደት በዓል (የፈረንጆቹ ገና) በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ላይ በዛሬው እለት በመከበር ላይ ይገኛል።
የእየሱስ ክርስቶስን ልደት ለማስታወስ በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎች የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች እያከናወኑ ነው።
በገና በዓል ዋዜማ የካቶሊኩ ጳጳስ ፍራንሲስ ቫቲካን ወስጥ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ “ያለንን ማካፈልና ለተቸገሩ መስጠት ተገቢ ነው” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት 2 ሺህ ሰዎች ብቻ በተገኙበት ቦታ በዓሉን ያከበሩት ፖፕ ፍራንሲስ፤ ለገና በዓል ማስዋቢያነት ከሚውሉ ብልጭልጮች እና መብራቶች ጀርባ ያሉ የተቸገሩ ሰዎችን መመልከት ይገባል ብለዋል።
የተለያዩ የዓለም ሀገራት መሪዎች በዓሉን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት እያስተላፉ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም፤ በመላው ዓለም የገና በዓልን ዛሬ እያከበሩ ለሚገኙ በሙሉ መልካም በዓል እንዲሆን መልካም ምኞታውን ገልፀዋል።
አሜሪካ እና አውሮፓን ጨምሮ በርካታ የዓለም ሀገራት የገና በዓልን ዛሬ የሚያከብሩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ 14 ሀገራት ድግሞ የእየሱስ ክርስቶስን ልደት በዓል (ገና) ታህሳህ 29 ያከብራሉ።
በዚህም መሰረት ከአፍሪካ፤ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ግብፅ በተለይ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች የገና በዓልን በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 እንዲሁም በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ ታኅሣሥ 28 ያከብራሉ።
እንዲሁም ሩስያ፣ ሰርቢያ፣ ቤላሩስ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ካዛኪስታን፣ እስራኤል፣ ቡልጋሪያ፣ መቄዶኒያ፣ ጆርጂያ እና ሞልዶቫም የገና በዓልን ታህሳስ 29 የሚያከብሩ ሀገራት ናቸው።