የሜሲ ሀገር አርጀንቲና የ36 ዓመት በኋላ ወደ ዋንጫው ለመመለስ ሳዑዲ አረቢያን ትገጥማለች
ሜክሲኮና ፓላንድ ምሽት 1 ስአት የሚያደርጉት ጨዋታም ከምድብ ሶስት ወደ ጥሎ ማለፉ የሚገቡ ሀገራትን ከወዲሁ ይጠቁማል
ከምድብ አራት ቱኒዚያ ከዴንማርክ፤ ፈረንሳይ ከአውስትራሊያ ዛሬ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ
ሶስተኛ ቀኑን የያዘው የአለም ዋንጫ ዛሬ የምድብ ሶሰት እና አራት ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።
ከምድብ ሶስት አርጀንቲና ከሳኡዲ አረቢያ ቀን 7 ስአት ፤ ፖላንድ ከሜክሲኮ ምሽት 1 ስአት ይፋለማሉ ከምድብ አራት ደግሞ ቱኒዚያ ከዴንማርክ ፤ ፈረንሳይ ከአውስትራሊያ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል
የሁለት ጊዜ የአለም ዋንጫ ሻምፒዮኗ አርጀንቲና ሳኡዲ አረቢያን በማሸነፍ ከ36 አመት በኋላ ዋንጫውን የማንሳት ጉዟዋን አሃዱ ለማለት አስባለች።
የመጨረሻ የአለም ዋንጫው ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የ36 አመቱ ሊዮኔል ሜሲም ጫናው በዝቶበታል።
በ1994 የአለም ዋንጫ 16 ውስጥ የገባችበት ውጤት የተሻለ ሆኖ የተመዘገበላት ሳኡዲ አረቢያ ለአርጀንቲና ቀላል ተጋጣሚ ትሆናለች ተብሎ አይጠበቅም።
ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም በተገናኙባቸው አራት ጨዋታዎች አርጀንቲና ሁለቱን አሸንፋ ቀሪዎቹ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።
በምድብ ሶስት አንደኛ ሆኖ ለማለፍ ሰፊ ግምት የተሰጣቸው ውሃ ሰማያዊና ነጭ መለያ ለባሾቹ በሉሳይል ስታዲየም አልሳቁሮቹን (አረንጓዴ ወፎች) 7 ስአት ላይ ይገጥማሉ።
በአለም ዋንጫው 18 ጊዜ ተሳትፋ የ1978ቱን እና የ1986ቱን ዋንጫ የወሰደችው አርጀንቲና ፤ የስድስት ጊዜ ተሳትፎ ካላት ሳኡዲ አረቢያ የሚያደርጉት ጨዋታ ያልተጠበቀ ውጤትም ሊመዘገብበት ይችላል።
ከምድቡ ሜክሲኮና ፖላንድ ምሽት 1 ስአት የሚያደርጉት ጨዋታም ከአርጀንቲና በመጠቀል ወደ ጥሎ ማለፍ የሚገባውን ቡድን ይጠቁማል ተብሏል።
በምድብ አራት ደግሞ ዴንማርክ ከአፍሪካዊቷ ቱኒዚያ ፤ ፈረንሳይ ከአውስትራሊያ ዛሬ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በአለም ዋንጫው አምስተኛውን ተሳትፎ የሚያደርገው የቱኒዚያ ብሄራዊ ቡድን የሚገጥመው በአለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ የሀገራት ደረጃ 10ኛ የተቀመጠችውን ዴንማርክ ነው የሚገጥመው።
ንስሮቹ በአለም ዋንጫ 15 ፍልሚያዎች ሁለቱን አሸንፈው በ9ኙ ተሸንፈዋል፤ ከምድባቸውም አልፈው አያውቁም። በኳታር የሚገኙ የሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ደጋፊዎች ይህ የቱኒዚያ ከተሳትፎ ያልዘለለ ውጤት እንዲለወጥ 10 ስአት ላይ በኢዱኬሽን ሲቲ ስታዲየም ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከምድቡ ቀዳሚዋ የማለፍ ግምት የተሰጣት ፈረንሳይ አውስትራሊያን 4 ስአት ላይ ትገጥማለች።