የማኔ አለመኖር በሴኔጋል ካምፕ ውስጥ ከፍተኛ ተጽእኖ መፍጠሩ እንደማይቀር እየተነገረ ነው
ሳዲዮ ማኔ ክለቡ ባየርን ሙኒክ በቅርቡ ቨርደር ብሬመንን 6-1 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ በጉዳት ከሜዳ መውጣቱን ተከትሎ በዓለም ዋንጫ ላይ የሚኖረው ተሳትፎ አጠራጣሪ እንዳደረገው አይዘነጋም።
በዚህም የተነሳ በሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን አሊዩ ሲሴ ቡድን ውስጥ የተካተተው ሳዲዮ ማኔን ከኳታሩ የዓለም ዋንጫ ውጪ ሊሆን እንደሚችል በርካታ ሚዲያዎች ሲዘግቡ ቆይተዋል።
የተፈራው አልቀረም የሳዲዮ ማኔን ህክምና ሲከታተል የቆየው የሃኪሞች ቡድን ማኔ በእግር ጉዳት ምክንያት ከዓለም ዋንጫ ውጪ መሆኑ አረጋግጧል ሲል ፎክስ ስፖርት ዘግቧል።
የቡድኑ መሪ ዶክተር ማኑዌል አፎንሶ በሴኔጋል ኦፊሴላዊ የትዊተር ገጽ ላይ ባጋሩት ቪዲዮ "እንደ አለመታደል ሆኖ የዛሬው [ሐሙስ] አም.አር.አይ እንደሚያሳየን ማሻሻያው እንዳሰብነው ጥሩ እንዳልሆነ እና በሚያሳዝን ሁኔታ ሳዲዮን ከዓለም ዋንጫ ማውጣት እንዳለብን ነው" ብለዋል።
ሳዲዮ ማኔ በቅርቡ ቀዶ ጥገና ማድረግ እንዳለበትም አክለዋል። አሁን ላይ የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ኳታር መድረሱ እየተነገረ ነው።
ብሄራዊ ቡድኑ ኔዘርላንድስ፣ ኢኳዶር እና ኳታር በሚገኙበት ምድብ 1 ላይ መደልደሉ ይታወቃል።
ቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከኔዘርላንድስ ፣ ከአራት ቀናት በኋላ ከአስተናጋጇ ኳታርን እንዲሁም የምድብ ሀ የመጨረሻ ጨዋታው ህዳር 29 ከ ኢኳዶር ጋር የሚያደረግ ይሆናል።
ያም ሆኖ የሳዲዮ ማኔ ጉዳት የዓለም ዋንጫ በይፋ ሊጀመር ጥቂት ሳምንታት ሲቀረው የተከሰተ እንደመሆኑ ለብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አሊዩ ሲሴ እና መላ ሴኔጋላዊያን አስደንጋጭ ዜና ሆኗል።
የማኔ አለመኖር በሴኔጋል ካምፕ ውስጥ ከፍተኛ ተጽእኖ መፍጠሩ አይቀርምም ነው የተባለው።
ማኔ እስካሁን በርካታ ዋነወጫዎችን ያነሳ እና 34 ጎሎችን በስሙ ያስቆጠረ መሆኑም ይታወቃል። ሰኔጋላዊው ኮከብ ሀገሩ የዘንድሮውን አፍሪካ ዋንጫ እንድታነሳ የነበርው ከፍተኛ ሚናም አይዘነጋም።
በክረምቱ በ35 ሚሊየን ፓውንድ ከሊቨርፑል ባየርን የተቀላቀለው ማኔ በጀርመን ባሳለፈው የመጀመርያ የውድድር ዘመን ለክለቡ ድንቅ ብቃት ማሰየት የቻለ ተጫዋችም ነው።
በሁሉም ውድድሮች 23 ጨዋታዎችን አድርጎ 11 ጎሎችን በማስቆጠር አራት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችንም አመቻችቷል።