“ከኮሮና ክትባቶች ጋር በተያያዘ ዓለም ‘አስከፊ’ የሞራል ውድቀት እየደረሰበት ነው”- ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር)
ድርጅቱ እንኳን መረጃ እያገኘ እንዳልሆነ እና መዘዙ በድሃ ሀገራት ላይ የከፋ እንደሚሆንም ተናግረዋል
የበለፀጉ ሀገራት የኮሮና ክትባቶችን ለራሳቸው ብቻ እያጋበሱ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል
ድሃ ሀገራት በሚሰቃዩበት ጊዜ የኮቪድ-19 ክትባቶችን የበለጸጉ ሀገራት በብቸኝነት የሚጠቀሙ ከሆነ ዓለም “በአሰቃቂ ሥነ ምግባራዊ ውድቀት አፋፍ ላይ ነች” ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዛሬ-ሰኞ ዕለት ተናግረዋ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ፣ የሀብታም ሀገራትን የ “እኔ-የመጀመሪያ” አስተሳሰብ በማውገዝ የበለፀጉ ሀገራት ለድርጅቱ ምንም መረጃ ሳያቀርቡ የክትባት አምራቾችን በማሳደድ በራሳቸው መንገድ ብቻ ለክትባቱ እየተሸቀዳደሙ ነው ብለዋል፡፡
የበለፀጉ ሀገራት በየራሳቸው መንገድ እየወሰዱ ያለው እርምጃ ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ክትባቱን በፍትሀዊነት ለማድረስ የነበረውን ተስፋ የሚያመነምን እንደሆነም ዶ/ር ቴድሮስ ገልጸዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ስብሰባን ለማስጀመር በጄኔቫ ባደረጉት ንግግር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ክትባቶችን በዓለም ዙሪያ በፍትሃዊ ተጠቃሚነት የማግኘት ተስፋ አሁን ከባድ አደጋ ላይ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ እንዳሉት ቢያንስ 49 ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ እስካሁን ድረስ 39 ሚሊየን የኮሮናቫይረስ ክትባት ተሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል “በአንድ ዝቅተኛ ገቢ ባለው ሀገር ውስጥ 25 ክትባት ብቻ ተሰጥቷል፡፡ 25 ሚሊዮን አይደለም; 25,000 አይደለም; 25 ብቻ” ብለዋል፡፡
“በግልጽ መናገር አለብኝ፡፡ ዓለም በከባድ የሞራል ውድቀት አፋፍ ላይ ነች - እናም የዚህ ውድቀት ዋጋ በዓለም ድሃ ሀገራት ውስጥ በሚኖሩ ህይወት እና ኑሮ ነው የሚከፈለው” ሲሉ መዘዙ በድሀ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል መናገራቸውን የዘገበው አል አረቢያ ነው፡፡