“የእሱን ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች ወደ ጦርነት በገቡ ጊዜ ከእሱ ምን ልትጠብቁ ኖሯል”- ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ስለ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የተናገሩት
“ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ወግኖ እነዚህን ሰዎች ያወግዛል ብለን አንጠብቅም”ም ነው ጄነራሉ ያሉት
“እነሱን ለመርዳት ያልቆፈረው ጉድጓድ የለም”
“እነሱን ለመርዳት ያልቆፈረው ጉድጓድ የለም”
የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሀኑ ጁላ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም “የዓለም አቀፍ ተልዕኮ ዕድሉን ተጠቅሞ የህወሓትን ጁንታ ለመርዳት ያላደረገው ጥረት የለም” ሲሉ ተናገሩ፡፡
ጄነራል ብርሀኑ ይህን የተናገሩት በህወሓት ላይ የተጀመረውን የህግ ማስከበር ወታደራዊ እርምጃ በማስመልከት ትናንት ለብዙሃን መገናኛዎች መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
“ሰውየው ራሱ የዛ ቡድን አባል፤ እንደምታውቁትም ማዕከላዊ ኮሚቴ ነው” ያሉት ጄነራሉ “የእሱን ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች ወደ ጦርነት በገቡ ጊዜ ከእሱ ምን ልጠብቁ ኖሯል” ሲሉ ነው የአለም አቀፉ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ድርጊት የሚጠበቅ እንደሆነ የገለጹት፡፡
“ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ወግኖ እነዚህን ሰዎች ያወግዛል ብለን እኛ አንጠብቅም” ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
“እነሱን ለመርዳት ያልቆፈረው ጉድጓድ የለም”ም ብለዋል ጎረቤት ሃገራት ጭምር ሳይቀር ጦርነቱን እንዲያወግዙ እና ህወሓትን በጦር መሳሪያ ጭምር እንዲደግፉ መቀስቀሱን በማስታወስ፡፡
“የዓለም አቀፍ ተልዕኮ እድሉን ተጠቅሞ ሰዎችን ለማሳመን ጥረት አድርጓል”ም ነው ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ያሉት፡፡
“ግን የሚሳካለት አይደለም፤ ይሳካለትም እንደሁ እናያለን” ብለዋል፡፡
ይህን ጥረት ያደረገው “የእነሱ አባል ወንጀለኛ” በመሆኑ እንደሆነም ጄነራል ብርሀኑ ተናግረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ይሄን እያደረጉ ለምን በተሰጣቸው ኃላፊነት ሊቀጥሉ እንደቻሉ ከጋዜጠኞቹ ለቀረበላቸው ጥያቄም ጄነራሉ “ይሄ የእኛ ስራ አይደለም የመንግስት ነው፤መንግስት የሚያደርገውን ያደርጋል” ሲሉ መልሰዋል፡፡
“ከጁንታው ኃይል ጋር ጁንታ ነው ብሎ የማስወገድ ስራ የመንግስት ነው” ነውም ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ያሉት፡፡
የዓለም አቀፉ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ግን እስካሁን ድረስ ስለ ጉዳዩ ያሉት ነገር የለም፡