የመጀመሪያው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የቁንጅና ውድድር 10 ተፎካካሪዎች ተለዩ
በወይዘሪት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለመፎካከር 1 ሺህ 500 በቴክኖሎጂው የተፈጠሩ “ቆነጃጅቶች” ተመዝግበው ነበር ተብሏል
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በሚዳኘው ውድድር ለአሸነፊዎች 20 ሺ ዶላር ሽልማት ተዘጋጅቷል
የሚሊየኖችን ስራ ይነጥቃል የሚል ስጋት የፈጠረው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወደ ቁንጅና ውድድሩም ገብቷል።
በሚያዚያ ወር ፋንቩይ በተባለ የአርቲሻል ኢንተለጀንስ ድረገጽ አማካኝነት የመጀመሪያው የሰው ሰራሽ አስተውሎት የቁንጅና ውድድር እንደሚካሄድ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም ከአሜሪካ፣ አፍሪካ፣ ደቡብ አሜሪካ፣ ህንድ፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና አውሮፓ 1 ሺህ 500 ቴክኖሎጂው የፈጠራቸው “ቆነጃጂት” ለውድድር ተመዝግበዋል።
ከሰሞኑም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስማቸው የገነነው አቲና ሎፔዝ እና ኢሚሊ ፔሌግሪኒ እና ፈጣሪዎቻቸው በሶስት መስፈርቶች የውድድሩን የመጨረሻ 10 ተወዳዳሪዎች መምረጣቸውን ሜትሮ አስነብቧል።
ከ10 ተወዳዳሪዎችም ሶስቱ ተለይተው በያዝነው ሰኔ ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በሚመራ የሽልማት ስነስርአት ይፋ ይደረጋሉ ተብሏል።
ለአሸናፊዎቹ በአጠቃላይ 20 ሺህ ዶላር ለሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን፥ አሸናፊዋ 5 ሺህ ዶላር እና 3 ሺህ ዶላር ዋጋ ያለው የስልጠና እድል ታገኛለች ብለዋል አዘጋጆቹ።
የውድድሩ አዘጋጅ ፋንቩይ መስራች ዊል ሞናንግ ውድድሩ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፈጠራ ለተሰማሩ ሰዎች የትውውቅ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በቴክኖሎጂ የተፈጠሩ ሴቶችን በውበታቸው ማወዳደር ተገቢ አይደለም፤ መስፈርቶቹና ምርጫውም አሳማኝ አይደለም የሚሉ ትችቶችን የማይቀበሉት ዊል ሞናንግ፥ ውድድሩ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት እውቅናን የሚሰጥና ሂደቱም በሰዎች ከሚከወነው ይበልጥ ተአማኒ መሆኑን በመጥቀስም ይከራከራሉ።
የቁንጅና ውድድሩን በወር ከ10 ሺህ ዶላር በላይ የምታስገኘው ኢታና ሎፔዝና ኢሚሊ ፔሌግሪኒ ላለፉት 10 አመታት የወይዘሪት ብሪታንያ ዳኛ ከሆኑት ሳሊ አን ፋውሴት ጋር ተጣምረው ይዳኙታል ተብሏል።
በመጀመሪያው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የቁንጅና ውድድር ለመፋለም ከ1 ሺህ 500 ተወዳዳሪዎች ለመጨረሻው ዙር የተመረጡትን 10 ተክኖሎጂው የፈጠራቸው “ቆንጆውች” ቀጥሎ ይመልከቱ፦
ዛራ ሻታቫሪ (ህንድ)
አን ከርዲ (ፈረንሳይ)
ኤይላ ሉ (ብራዚል)
ኢሊዛ ካን (ባንግላዲሽ)
አሴና ኢሊክ (ቱርክ)
ኬንዛ ላይሊ (ሞሮኮ)
ላሊና (ፈረንሳይ)
ሰረን ኤይ (ቱርክ)
ኤያና (ሮማኒያ)
ኦሊቪያ ሲ (ፖርቹጋል)