የቁንጅና ውድድር መስፈርቱ ምንድን ነው? ያስባለችው "የአላባማ ወይዘሪት"
የ23 አመቷ ሳራ ሚሊከን ደስታዋን ማጣጣም ሳትጀምር “ከልክ ላለፈ ውፍረት ድጋፍ መስጠት ነው” ያሉ ሰዎች በውድድሩ አዘጋጆች ላይ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው
ደጋፊዎቿ ደግሞ ውድ የውበት መጠበቂያ ቁሳቁሶችና ልብሶችን በመላክ አጋርነታቸውን አሳይተዋታል
በአሜሪካ አላባማ ግዛት በተካሄደ የቁንጅና ውድድር አሸናፊ የሆነችው እንስት አነጋጋሪ ሆናለች።
የ23 አመቷ ሳራ ሚሊከን ከልክ ያለፈ ውፍረቷ ነው በውድድሩ አሸናፊ ሆናለች ስትባል ትችት ያስከተለባት።
የአሜሪካ ብሄራዊ የቁንጅና ውድድር አዘጋጁ አካልም በማህበራዊ ሚዲያዎች ተቃውሞ እያስተናገደ ነው።
ቁንጂና እንደተመልካቹ አይን ቢሆንም የአለባማዋ ቆንጆ ወፍራም መሆኗ የውድድሩን አዘጋጅ “ከልክ ላለፈ ውፍረት ድጋፍና እውቅና መስጠት ነው” ያሉ ሰዎች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።
የአሜሪካ ብሄራዊ የቁንጅና ውድድር አዘጋጅ (ኤንኤኤም) ተወዳዳሪዎች ራሳቸውን ሆነውና የተፈጥሮ ውበታቸውን እንዳያፍሩበት እንደሚያበረታታ በድረገጹ አስፍሯል።
ተወዳዳሪዎች ህልምና ተስፋቸውን በቃለመጠይቅ ከገለጹ በኋላ ለተመልካቾች የሚያደርጉት ገለጻ ብሎም ለማህበረሰባቸው የሚያደርጉት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዋነኛ መመዘኛ መስፈርት መሆናቸውንም ይጠቅሳል።
ሳራ ሚሊኪን የአላባማ ቆንጆ ተብላ የተመረጠችውም “በስብእናዋ፣ በከፍተኛ የራስ መተማመን እና የመግባባት ክህሎቷ” ነው ብሏል።
የረጅም ጊዜ ህልሟ መሳካቷ የፈጠረባት ደስታን የሚያደበዝዙ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ የተከፈተባት ሳራ ሚሊከን፥ “ደስታዬ ከአምስት ደቂቃ አልበለጠም፤ የሚሰብሩ ቃላት ይወረወሩብኝ ነበር” ብላለች።
“ሁሌም መልካም ነገሮችን ማንጸባረቅና አዎንታዊ ነገሮችን ማድረግ እፈልጋለው” የምትለው ሳራ፥ የቁንጅና ውድድር ማሸነፏ አስቀያሚ አስተያየቶች እንዲደርሷት ቢያደርግም አይዞሽ ያሏትም ቀላል አይደሉም።
በአጭር ጊዜ በፌስቡክና ኢንስታግራም በሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮችን ማፍራት የቻለች ሲሆን፥ በርካቶች ውድ የውበት መጠበቂያ ቁሳቁሶችና ልብሶችን በመላክ ፍቅራቸውን እንዳሳዩዋት ተናግራለች።
“የሰውነትህ ቅርጽና ክብደት ምንም ይሁን፤ ከየትም አካባቢ ና፤ በአዕምሮህ ሁሉንም ማድረግ ትችላለህ” የሚለው ንግግሯን የሚያጣቅሱ ደጋፊዎቿ የቁንጅና ውድድር ሃሳብን ያልተረዱ ሰዎች የሚሰጧቸውን አስተያየቶች በመቃወም አጋርነታቸውን እያሳዩዋት ነው።