ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴአና የአሜሪካ ፕሬዝዳንብ ባይደንን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሀገራት መሪዎች ለንደን ገብተዋል
ብሪታንያን ላለፉት 70 ዓመታት በንግስትነት ያገለገሉት ንግስት ኤልሳቤት ዳግማዊ በተወለዱ 96 ዓመታቸው በህመም ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
ህይወታቸው ያለፈው የንግስት ኤልሳቤት አሰከሬን ላለፉት 10 ቀናት በተለያዩ የብሪታንያ አደባባዮች እየተዘዋወረ የሀገሪቱ ዜጎችም ሀዘናቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
በነገው ዕለትም የንግስቲቱ ስርዓተ ቀብር እንደሚፈጸም ቢቢሲ የዘገበ ሲሆን በዚህ ብሄራዊ ስርዓተ ቀብር ፕሮግራም ላይ ከ200 የዓለማችን ሀገራት የተውጣጡ ከ500 በላይ መሪዎች እና ተወካዮች ይገኛሉም ተብሏል።
በርካታ የዓለማችን መሪዎች ወደ ለንደን በማምራት ላይ ሲሆኑ፤ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በንግስት ኤልሳቤጥ ቀብር ላይ ለመታደም ትናንት ለንደን ገብተዋል።
የኬንያ ፕሬዜዳንት ዶ/ር ዊሊያም ሩቶ፣ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ፣ የሱዳን ጦር አዛዥ እና የሃገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን እና የደቡብ አፍሪካው ፐሬዝዳንት ስሪል ራማፎሳም ለንደን ገብተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ፣ የቻይና ምክትል ፕሬዝዳንት ዋንግ ቂሻን ፣የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ፣ የኒውዝላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደን እና ሌሎችም አስቀድመው ለንደን ደርሰዋል ተብሏል።