አሜሪካ አፈትልኮ ስለወጣው የዩክሬን ጦርነት ሰነድ ማጣራት እንዲደረግ አዘዘች
ሚስጢራዊ ሰነዶቹ ከዩክሬን ጦርነት ባሻገር በእስራኤል እየተካሄደ ስለሚገኘው ተቃውሞና የሞሳድ ሚና ጥብቅ መረጃዎችን ይዘዋል ተብሏል
አፈትልከው ወጡ የተባሉት ሚስጢራዊ ሰነዶች ከዋሽንግተን እስከ ኬቭ፤ ከቴል አቪቭ እስከ ሴኡል መነጋገሪያ ሆኗል
አሜሪካ በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተዘዋወሩ የሚገኙ እጅግ ሚስጢራዊ የሆኑ ሰነዶች በማንና እንዴት እንደወጡ ይጣሩ ዘንድ ማዘዛ ተገልጿል።
ዋይትሃውስ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት (ፔንታጎን) ጉዳዩን እንዲያጣራ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ፔንታጎን በበኩሉ አፈትልከው ወጡ የተባሉትን ሰነዶች፣ ካርታዎች እና ፎቶግራፎች ትክክለኛነት እየመረመረ መሆኑን ትናንት ይፋ አድርጓል።
ሚስጢራዊ ሰነዶቹን ባወጡ አካላት ላይ የወንጀል ክስ ከመሰረተው የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴርም እየተነጋገረ መሆኑን መግለጹን ሬውተርስ ዘግቧል።
ባለፈው ሳምንት ኒውዮርክ ታይምስ ይዞት በወጣው ዘገባ የዩክሬንን ጦርነት ጨምሮ በርካታ የአሜሪካ ሚስጢራዊ ሰነዶች አፈትልከው መውጣታቸው ተመላክቷል።
ከዚህ ዘገባ አስቀድሞ ግን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሰነዶቹ ሲዘዋወሩ ቆይተውል ነው የተባለው።
አሁንም ድረስ የማጣራት ስራው የቀጠለና ስለትክክለኛነታቸው ዋሽንግተን ማረጋገጫ ያልሰጠችባቸው እጅግ ጥብቅ መረጃዎችን የያዙት ሰነዶች በማንና እንዴት ወጡ የሚለው አልታወቀም።
ሚስጢራዊ ሰነዶቹ ምን ይላሉ?
በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲዘዋወሩ የሰነበቱት ሚስጢራዊ ሰነዶች ከዩክሬን ጦርነት እስከ እስራኤል ተቃውሞ በርካታ መረጃዎችን ይዘዋል።
የዩክሬን ጦርነት የሚመራበትን ስትራቴጂ፣ የኬቭ ወታደራዊ አቅም እና ውስንነቶች፣ የወታደራዊ ስልጠና እቅዶችና ተያያዥ መረጃዎች የሚያነሱት ሰነዶች በጦርነቱ በሩሲያ እኛ ዩክሬን በኩል ህይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ቁጥር ያመላክታሉ ተብሏል።
በሞስኮ ከ189 ሺህ እስከ 223 ሺህ ወታደሮች መገደላቸውን አልያም መቁሰላቸውን የሚጠቅሱት ሰነዶች፥ በኬቭ በኩል የደረሰውን ጉዳት ከ124 ሺህ እስከ 131 ሺህ እንደሚገመት ያስቀምጣሉ ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።
የአሃዙ አጠራጣሪነትን የሚጠቅሰው ፔንታጎን እስካሁን የሰነዶቹን ትክክለኛነት ባያረጋግጥም “ሆን ተብሎ” የተቀየረ ነገር እንደሚኖር ግን ገልጿል።
የዩክሬንን የአየር ሃይል ውስንነት የሚያነሱ “ሚስጢራዊ ሰነዶች”ም ኬቭ ከምዕራባውያኑ ቃል የተገባላት የጦር መሳሪያዎች በፍጥነት መድረስ እንዳለባቸው ያመላክታሉ።
ይፋ የተደረጉት ሰነዶች በእስራኤል እየተካሄዱ ካሉ ተቃውሞዎችን የስለላ ድርጅቱ ሞሳድ እያበረታታ መሆኑን ዋሽንግተን በስለላ እንደደረሰችበት አሳይተዋል ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን መሰረተ ቢስ በሚል አጣጥለውታል።
የደቡብ ኮሪያ መንግስት ለዩክሬን ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ሊደረግ ስለሚገባው ጫና የሚያመላክቱ ናቸው የተባሉ ሰነዶችም ወጥተዋል።
ሰነዶቹን የሩሲያ አልያም ዩክሬን ደጋፊዎች ሳያወጧቸው አይቀርም የሚሉ ተንታኞች አሉ።
ከ50 በላይ የሚሆኑ “ጥብቅ ሚስጢር” ይዘዋል የተባሉትን ሰነዶች ተመልክቻለሁ ያለው ሬውተርስ ግን፥ ካፈተለኩት ሰነዶች ጀርባ ማን አለ የሚለው ከአሜሪካውያን የሚዘል እንዳልሆነ ተንታኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ዋይትሃውስ ግን ወጡ የተባሉት ሰነዶች ላይ ፈጣን ማጣራት ተካሂዶ ዝርዝር ሪፖርት እንዲወጣ ማዘዙ ነው የተገለጸው።