ኢትዮጵያውያን በ2024 በቀዳሚነት የመረጡት የሙያ ዘርፍ የትኛውን ነው?
የሀገራት ዜጎች በበይነመረብ የጠይቋቸውን ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ በወጣ ጥናት አውሮፕላን አብራሪ (ፓይለት) ቁጥር 1 ሆኗል
የህክምና፣ መምህር እና ጥብቅና ሙያዎችም እስከ 10ኛ ባለው ደረጃ ውስጥ ተካተዋል
በልጅነታችን ወደፊት ምን መሆን ትፈልጋለህ ለሚለው የመምህራኖቻችን ጥያቄ አብዛኞቻችን የምንሰጠው ምላሽ አውሮፕላን አብራሪ ወይም ዶክተር የሚል ነበር።
አሁን ላይ ግን “ዩቲዩበር”፣ “የስነልቦና አማካሪ” አልያም ሌላ የሙያ ዘርፍ ላይ መሰማራት እንደሚፈልጉ የሚገልጹ ህጻናትን መመልከት እየተለመደ ነው።
የጎግል ፍለጋ ውጤቶችን በመተንተን መረጃዎችን የሚያጋራውን “አሽረፍስ” የተባለ ድርጅትን ዋቢ ያደረገው ጆብሲከር ድረገጽ በ2024 በአለማቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሙያ ዘርፎችን ይፋ አድርጓል።
ድረገጹ በቀዳሚነት ያስቀመጠው አውሮፕላን አብራሪነትን (ፓይለት) ነው። በበይነመረቦች “አውሮፕላን አብራሪ መሆን እንዴት ይቻላል?” የሚለው ጥያቄ በጥር ወር 2024 ብቻ ከ50 ሺህ ጊዜ በላይ ተጠይቋል።
ብሪታንያ፣ ስፔን፣ አየርላንድ፣ ኒውዝላንድ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ህንድ፣ ሳኡዲ አረቢያ እና ጃፓንን ጨምሮ በ55 ሀገራት ቀዳሚ የሆነው ጥያቄ የአውሮፕላን አብራሪነትን የአለማችን ቀዳሚው ተፈላጊ ስራ ያደርገዋል።
ኢትዮጵያውያንም በቀዳሚነት የመረጡት የሙያ ዘርፍ አውሮፕላን አብራሪነትን መሆኑን ጥናቱ ያሳያል።
ጆብሲከር በሁለተኛነት ያስቀመጠው የበረራ አስተናጋጅነት (ሆስተስ) ሙያን ነው። ስለዚህ ሙያ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በጥር ወር 29 ሺህ የበይነመረብ ፍለጋ ተካሂዷል።
በአለማቀፍ ደረጃ ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች ተጨማሪ ማብራሪያ የጠየቁበት የሞዴልነት ሙያ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሙያው በፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ስዊድን፣ ግብጽ፣ አልጀሪያ፣ ኢራቅ እና ሞሮኮ ቁጥር 1 ተፈላጊ የስራ ዘርፍ ነው ተብሏል።
የስነልቦና ጉዳዮች አማካሪነት እና በማህበራዊ ሚዲያዎች ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።
በኡጋንዳ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቀዳሚ የሆነው የህክምና ባለሙያ (ዶክተር) ሙያ እና በቤላሩስ፣ ዩክሬን እና ሩሲያ ቁጥር አንድ ተወዳጁ ሙያ መምህርነት በአለማቀፍ ደረጃ ስድስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የጥብቅና ሙያ ደግሞ ስምንተኛ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፥ በሃይቲ እና ላይቤሪያ ቀዳሚው ተፈላጊ ዘርፍ ነው ተብሏል።
በጥር ወር አውዳሚ የእሳት አደጋዎችን በመቆጣጠር የስራ ዘርፍ ለመሰማራት ምን ያስፈልጋል? የሚሉና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎች መቅረባቸውን የጠቀሰው ጆብሲከር፥ ይህ ሙያ በቺሊ ቁጥር አንድ ተፈላጊና በአለማቀፍ ደረጃ ደግሞ 9ኛ ላይ ተቀምጧል ብሏል።
በድረገጹ 10ኛ ሆኖ የተቀመጠው “ስራፈጣሪ” ወይም ኢንተርፕርነር ነው፤ በራሳቸው ስራ መፍጠር የሚፈልጉ ሰዎች እየተበራከተ መምጣት አበረታች ነው ብሏል ጆብሲከር።
የባልካኗ ሞንቴኔግሮ ዜጎች የህይወት ዘመን ግባቸው ሙዚቀኛ መሆን ነው ፤ የኡራጓይ እና ፊጂ ዜጎች ደግሞ “ዩትዩበር” በመሆን ህይወታቸውን ማቃናት ይሻሉ ነው የተባለው።
የሊዮኔል ሜሲ ሀገር አርጀንቲና ዜጎች በበይነ መረብ አብዝተው የሚጠይቁት ከምግብ ዝግጅት (ሼፍ) ጋር የተያያዙ ናቸው፤ የእግርኳስ አሰልጣኝ የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው የፓራጓይ ዜጎች ናቸው ይላል የጆብሲከር መረጃ።
ቻይናውያን ፓይለት ወይም ሞዴል ቀዳሚ ምርጫ በሆነበት የእስያ አህጉር የተለየ የሙያ ፍቅር አሳይተዋል፤ ቀዳሚው ምርጫቸው የጋዜጠኝነት ሙያ ነው።
ቤጂንግ የሉአላዊ ግዛቴ አካል ናት በምትላት ታይዋን ደግሞ መምህርነት ተመራጩ ሙያ ሆኗል።
ጦርነት ባደቀቃቸው አፍጋኒስታን እና የመን ተመራጩ የሙያ ዘርፍ ጸሃፊነት መሆኑም ነው የተጠቆመው።
ጆብሲከረ ጥናቱ የበይነመረብ ፍለጋ ውጤቶችን ብቻ መሰረት በማድረግ የወጣ መሆኑ ይሰመርበት ብሏል።
aXA6IDE4LjIyMi44MC4xMjIg ejasoft island