የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት 223 ሺህ ዶላር፤ የኬንያው 192 ሺህ ዶላር ዓመታዊ ደመወዝ ይከፈላቸዋል
ፖለቲከኞች በምርጫ ቅስቀሳ የተለያዩ ቃሎችን ከገቡ በኋላ እና የመራጮችን ድምጽ ካገኙ በኋላ አንድን ሀገር በፕሬዝዳንት እና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለግላሉ፡፡
ብዙ ጊዜም መሪዎች ለህዝብ ጥቅም እንደሚሰሩ ቢናገሩም ብዙዎች የግል ጥቅማቸውን እንደማይረሱ ይታወቃል።
ዓለማችን 213 ሀገራት ያሏት ሲሆን ከነዚህ ሀገራት መሪዎች መካከል ከፍተኛ ደመወዝ የሚከፈለው ማን ነው የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።
እንደ ዩኤስኤ ቱዳይ ዘገባ ከሆነ የሲንጋፖሩ ጠቅላይ ሚኒስትር በዓመት ሁለት ሚሊዮን ዶላር የሚከፈላቸው ሲሆን ከዓለማችን መሪዎች መካከል ከፍተኛ ተከፋዩ መሪ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ13 ወራት ቦነስ ክፍያን እና ጥቅማ ጥቅሞችን ጨምሮ በአጠቃላይ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ይከፈላቸዋል ተብሏል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ደግሞ በዓመት 204 ሺህ እንደሚከፈላቸው ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
በአጠቃላይ በዓለማችን ካሉ መሪዎች መካከል ዝቅተኛው 150 ሺህ ዶላር ከፍተኛው ደግሞ 2 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፈላቸው ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የስዊዘርላንዱ ፕሬዝዳንት ገይ ፓርሜሊን ደግሞ 442 ሺህ ዶላር ዓመታዊ ደመወዝ ሲከፈላቸው የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ደግሞ 366 ሺህ ዶላር ይከፈላቸዋል።
እንዲሁም የአይስላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር 317 ሺህ ዶላር ሲከፈላቸው የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ 216 ሺህ ዶላር እንደሚከፈላቸው ዘገባው አክሏል፡፡
በአውሮፓ የፖላንዱ ፕሬዝዳንት 55 ሺህ ዶላር በመከፈል ዝቅተኛው የአህጉሪቱ ተከፋይ የሀገር መሪ ሲሆኑ የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክተር ኦርባን 62 ሺህ ዶላር ይከፈላቸዋል ተብሏል፡፡
ከአውሮፓ ስንወጣ ደግሞ የካሜሩኑ ፕሬዝዳንት ፖል ቢያ ከአፍሪካ ትልቁ ተከፋይ መሪ ናቸው፡፡ ፕሬዝዳንት ፖልቢያ በዓመት 620 ሺህ ዶላር በደመወዝ መልክ ይከፈላቸዋል፡፡
ከፖል ቢያ በመቀጠል የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፖሳ 223 ሺህ ዶላር የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሮ ኬንያታ 192 ሺህ ዶላር ዓመታዊ ደመወዝ ይከፈላቸዋል ተብሏል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ደግሞ 400 ሺህ ዶላር በዓመት የሚከፈላቸው ሲሆን የአንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ደግሞ 200 ሺህ ዶላር እንደሚከፈላቸው ተገልጿል።