ለዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት 2 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ
ዓለም በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር ለማዋጣት ብታስብም ይህ ግን በቂ አይሆንም ተብሏል
የዘንድሮው የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ኮፕ28 ጉባኤ በሚቀጥለው ወር በአረብ ኢምሬት ይካሄዳል
ለዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት 2 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ፡፡
ዓለማችን በየጊዜው በየአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት እየተፈተነች ሲሆን የምድራችን ከፍተኛው ሙቀት በዘንድሮው ዓመት ተመዝግቧል፡፡
ይህ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ከ2 ነጥብ 4 ትሪሊዮን በላይ ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡
የዘንድሮው የአየር ንብረት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ወይም ኮፕ28 አዘጋጅ የሆነችው የተባበሩት አረብ ኢምሬት ስትሆን ጉባኤው ከአንድ ወር በኋላ በዱባይ ይካሄዳል፡፡
የኮፕ28 ፕሬዝዳንት እንዲሁም የአረብ ኢምሬት ኢንዱሰትሪ እና አድቫንስድ ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የሆኑት ዶክተር ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃቢር እንዳሉት ዓለም እየደረሰባት ላለው የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት ከ2 ነጥብ 4 ትሪሊዮን በላይ ዶላር ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡
በ50 ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት በአፍሪካ
በአየር ንብረት ለውጥ የበለጠ ተጎጂ የሆኑት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ናቸው ያሉት ዶክተር ሱልጣን ዓለማችን በ2030 ለአየር ንብረት ለውጥ የሚስፈልጋት ገንዘብ ከ2 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ተቋማት እና በጎ ፈቃደኞች በዓመት 100 ቢሊዮን ዶላር ለማዋጣት ያቀዱ ቢሆንም ይህ ገንዘብ በቂ እንዳልሆነም ዶክተር ሱልጣን አል ጃቢር አክለዋል፡፡
በመሆኑም ዓለም እየደረሰበት ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ተጨማሪ ሀብት ማሰባሰብ የሚያስችል ስርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
ዶክትር ሱልጣን አልጃቢር ዓለም የተባለውን ገንዘብ መሰብሰብ ትችላለች? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም አዎ ሱሉ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ይሁንና መንግስታት እና የግል ተቋማት ለጉዳዩ ትኩረት ከሰጡ ይሳካል ብለዋል፡፡
የበለጸጉ ሀገራትም ከዚህ በፊት ከኢንዱስትሪዎቻቸው በሚለቋቸው በካይ ጋዞች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ታዳጊ ሀገራት ለመስጠት ያሰቡትን የ100 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ እንዲሰጡም አሳስበዋል፡፡