የዓለም ህዝብ ቁጥር ከአራት ወራት በኋላ 8 ቢሊዮን ይደርሳል ተባለ
ከ50 ዓመት በኋላ የዓለማችን ህዝብ ቁጥር ከ10 ቢሊዮን በላይ ይሆናል ተብሏል
ሕንድ ከአንድ ዓመት በኋላ ቻይናን በመብለጥ የዓለማችን ባለብዙ ህዝብ ቁጥር ባለቤት ትሆናለች
የዓለም ህዝብ ቁጥር ከአምስት ወራት በኋላ 8 ቢሊዮን ይደርሳል ተባለ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) እንዳለው ከሆነ የፊታችን ህዳር አጋማሽ ወር ላይ የዓለማችን ህዝብ ቁጥር ስምንት ቢሊዮን እንደሚደርስ አስታውቋል፡፡
የተመድ ትንበያ እንዳሳወቀው አሁን ላይ የዓለማችን ባለብዙ ህዝብ ቁጥር የሆነችው ቻይና ከአንድ ዓመት በኋላ በህንድ ብልጫ ሊወሰድባት እንደሚችል በትንበያው አስታውቋል፡፡
የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በትዊተር ገጻቸው እንዳሉት ሁላችንም ለምንጋራት ዓለማችን የበኩላችንን ማድረግ አለብን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላለፈዋል፡፡
ዓለማችን ብዝሃነትን የምታስተናግድ እና ለሁላችን ምቹ እንድትሆን የህጻናትን እና እናቶች ሞትን ማስቀረት የሚያስችሉ ስራዎችንም ማከናወን አለብን ሲሉ ዋና ጸሃፊው አሳስበዋል ሲል ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
የዓለማችን የውልደት መጠን እድገት አሁን ላይ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ያለው ተመድ ዓመታዊ የውልደት መጠን እድገቱ ከ1950 ወዲህ ዝቅተኛው እንደሆነም ተመድ አስታውቋል፡፡
የዓለም ህዝብ ቁጥር በ2030 8 ነጥብ 5 ቢሊዮን በ2050 ደግሞ 9 ነጥብ 7 ቡሊዮን እንዲሁም በ2080 ደግሞ የዓለማችን ህዝብ ቁጥር 10 ነጥብ 4 ቢሊዮን እንደሚደርስ ተመድ በትንበያ ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ለወትሮው ከፍተኛ የውልደት መጠን ያስመዘግቡ የነበሩት ታዳጊ ሀገራት አሁን ላይ ዓመታዊ የውልደት መጠኑ እየቀነሰ መምጣቱንም ተመድ ጠቁሟል፡፡
ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ግብጽ፣ ኢትዮጵያ፣ ህንድ፣ ናይጀሪያ፣ ፓኪስታን፣ ፊሊፒንስ እና ታንዛኒያ በዓለማችን ህዝብ ቁጥር ላይ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡