ብላክ አይቮሪ፣ፊንካ ኤል ኢንጀርቶ እና ሀሴንዳ ላ ኢስሜራልዳ የተሰኙት የቡና ምርቶች በዓለማችን ውድ ከሚባሉት ውስጥ ናቸው
በኪሎ እስከ አንድ ሺህ ዶላር ድረስ የሚሸጥ ቡና እንዳለ ያውቃሉ?
ከውሃ ቀጥሎ ሰዎች ገዝተው የሚጠጡት ቡና በየጊዜው ዋጋው እየጨመረ ይገኛል፡፡
የዓለማችን ዋነኛ ቡና አምራች ከሆኑ ሀገራት መካከል የሚጠቀሱት ብራዚል እና ቬትናም በጎርፍ እና በድርቅ መመታታቸው በዓለም ቡና ዋጋ ላይ አሉታዊ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ግን በተለየ መንገድ የሚመረቱ የቡና ምርቶች ዋጋቸው በጣም ውድ ነው፡፡
ሲኤንቢሲ በተለየ መንገድ የሚመረቱ እና ዋጋቸው እጅግ ውድ የሆኑ የቡና ምርቶችን ይፋ አድርጓል፡፡ በኪሎ እስከ 1 ሺህ ዶላር በመሸጥ እና ዓለማችን ውድ ዋጋ የሚባለው በታይላንድ የሚመረተው ብላክ አይቮሪ ቡና ነው፡፡
ይህ የቡና ምርት ቡናውን ዝሆን እንዲመገበው በማድረግ ከተጸዳዳው በኋላ የሚገኘው የቡና አይነት ነው ተብሏል፡፡
ሌላኛው ልዩ እና ውድ የሚባለው ቡና ፊንካ ኤል ኢንጀርቶ እና ሀሴንዳ ላ ኢስሜራልዳ የሚባሉት ሲሆን እነዚህ ምርቶች በኪሎ 350 እስከ 500 ዶላር ይሸጣሉ፡፡
ሌላኛው ውድ የሚባለው ቡና በኢንዶኔዢያ የሚመረት ሲሆን ይህም ድመት መሳይ እንስሳት ቡናውን እንዲመገቡት እና እንዲጸዳዱት ከተደረገ በኋላ የሚገኘው ሲሆን ልዩ ጣዕም ያለው ቡና ነው ተብሏል፡፡
መሰል የቡና አይነቶች የተለየ ልፋት እና ዘዴን የሚጠይቁ በመሆኑ ለውስን እና ቅንጡ ገበያዎች ካልሆነ በስተቀር በብዛት ለገበያ አይቀርቡም፡፡