ዋነኛ የቡና አምራች የሆኑት ብራዚል እና ቬትናም በድርቅ እና ጎርፍ መጠቃታቸው ለቡና ዋጋ መጨመር ዋነኛ ምክንያት ሆኗል
የዓለም ቡና ዋጋ በታሪክ ከፍተኛው ላይ ደረሰ፡፡
ከውሃ ቀጥሎ ሰዎች ገዝተው የሚጠጡት ቡና በየጊዜው ዋጋው እየጨመረ ይገኛል፡፡
የዓለማችን ዋነኛ ቡና አምራች ከሆኑ ሀገራት መካከል የሚጠቀሱት ብራዚል እና ቬትናም በጎርፍ እና በድርቅ መመታታቸው በዓለም ቡና ዋጋ ላይ አሉታዊ አስቷጽዖ አድርሷል፡፡
በዚህ ምክንትም አሁን ላይ አንድ ኪሎ ቡና በዓለም ገበያ ላይ በ6 ነጥብ 8 ዶላር እየተሸጠ ሲሆን ኢትዮጵያ የምታመርተው ኮፊ አረቢካ የሚባለው የቡና ዝርያ ደግሞ ውድ ምርት ሆኗል፡፡
በቬትናም እና ብራዚል ካጋጠመው የአየር ንብረት ለውጥ በተጨማሪም የቡና ጠጪዎች ቁጥር መጨመር፣ ቡናን ከተለያዩ ምርቶች ጋር በመቀላቀል ተጨማሪ ምርቶችን ማምረት እየተለመደ መምጣት ሌላኛው ለቡና ዋጋ መናር በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡
እንደ ኒስ ካፌ እና መሰል የቡና አቀነባባሪ የሆኑ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በቡና ዋጋ መናር ምክንያት መማረራቸውን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም በቻይና የቡና ጠጪዎች ቁጥር ከየትኛውም ሀገር በላይ ከፍተኛ ሆኗል የተባለ ሲሆን ሀገሪቱ ከአፍሪካ እና ሌሎች አህጉራት ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ወደ ሀገሯ አስገብታለች ተብሏል፡፡
ከ10 ዓመት በፊት አንድ ኪሎ ቡና ከሶስት ዶላር በታች የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ከእጥፍ በላይ አድጓል፡፡
የቡና ጠጪዎች ቁጥር እድገት አሁን ባለበት ፍጥነት የሚቀጥል ከሆነ የዋጋ መናሩ ሊጨምር እንደሚችልም ቢቢሲ ዓለም አቀፍ የቡና አቀነባባሪ ኩባንያዎችን አነጋግሮ በሰራው ዘገባ ላይ ጠቅሷል፡፡