ቡና መጠጣት የልብ እና ታይፕ 2 ስኳር በሽታዎችን እንደሚከላከል ጥናት አመላከተ
ካፊን መጠኑ ሳይበዛ ከማነቃቀት ባለፈ የጤና ጥቅም እንዳለው ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል
ጥናቱ በቀን ከ200-300 ሚሊግራም ካፊን በሚጠቀሙ ሰዎች በበሽታ የመያዝ እድላቸው 48.1 በመቶ ዝቅ ያለ ነው ብሏል
ቡና ሰዎችን ከማነቃቃት ባለፈ በተገቢው መጠን እና ልክ ከተወሰደ በተለይ ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያዙ በሽታዎችን ለመከላከል እንደሚረዳ አዲስ ጥናት አመላክቷል፡፡
በቻይናው ሺዡ ዩኒቨርስቲ የተጠናው ጥናት እንደሚያመላክተው በቀን ሶስት ስኒ ቡና መጠጣት ኢ-መደበኛ የልብ ምትን ማስተካከል እንዲሁም የልብ እና የታይፕ 2 የስኳር በሽታዎችን እንደሚከላከል አመላክቷል፡፡
ተመራማሪዎቹ 180 ሺህ ሰዎችን ለናሙና የወሰዱ ሲሆን የጥናቱ ተሳታፊዎች በቀን የሚሰውድት የካፊን መጠን ፣ የስራቸው ባህሪ እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የማድረግ ልምዳቸው በጥናቱ ውስጥ ተካቷል፡፡
በዚህም በቀን ሶስት ስኒ ቡና ወይም አረንጓዴ ሻይ የሚጠጡ ሰዎች ከማይጠጡት በተሻለ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችን የመከላከል አቅም አሳይተዋል ተብሏል፡፡
በቀን ሶስት ሲኒ የሚጠጡ ወይም ከ200-300 ሚሊግራም ካፊን በሚጠቀሙ ሰዎች ዘንድ በበሽታ የመያዝ እድላቸው 48.1 በመቶ ዝቅ ያለ ነው፡፡
ተመራማሪዎቹ በካፊን ውስጥ የሚገኘው ንጥረ ነገር የተጠቀሱትን በሽዎች በመከላከል በኩል ያለው አስተዋጽኦ ከምን እንደመነጨ ለማወቅ ተጨማሪ ምርመራዎችን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በጥናቱ የልብ እና የስኳር በሽታ ተጋላጭነትን ለመከላከል የሚያግዘው በካፊን ውስጥ የሚገኘው ንጥረ ነገር የሚታወቅ ከሆነ ለመድሀኒት ምርት እና ለተጨማሪ ምርመራዎች ሊያግዝ እንደሚችል ተመራማሪዎቹ ተስፋ አድርገዋል፡፡
ባለፉት አመታት ከቡና ጋር ተያይዘው የሚወጡ ጥናቶች ከፊሎች ቡናን አብዝቶ መጠቀም ለልብ ድካም እና ለሌሎችም ተያያዥ በሽታዎች እንደሚጋልጥ ሲናገሩ በአንጻሩ በሽታን የመከላከል አቅም እንዳለው የሚናገሩ ቀደም ብለው የወጡ ጥናት ውጤቶችን ውድቅ የሚያደርጉ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡
በተመሳሳይ በ2023 በአውስትራሊያ ተመራማሪዎች የወጡ የምርምር ውጤቶች የቡናን የጤና ገጸ በረከቶች የሚደግፉ ነበሩ፡፡
በዚሁ አመት ለንባብ የበቁ ሶስት የጥናት ውጤቶች ቡና የሰዎችን የበሽታ መከላከል አቅም እንዲሁም የአተነፋፈስ ስርአት እና የደም ዝውውርን ከሚያሻሻሉ ነገሮች መካከል አንዱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
እነኚህ ጥናቶች የ500 ሺህ ሰዎችን የ10 አመት የጤና ሪከርድ የተከታተሉ ሲሆን ቡና የማዘውተር ልምዳቸውን እና የበሽታ ተጋላጭነታቸውን መርምረዋል፡፡
በዚህም ስትሮክ ፣ የልብ ምት ፣ እና ሌሎችም የመተንፈሻ በሽታዎች የመጋለጥ ደረጃቸውን በመለካት ቡና አዘውትረው የሚጠጡ ሰዎች ለተጠቀሱት በሽታዎች ያላቸው ተጋላጭነት የቀነሰ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡