በዓለም ዙሪያ ከ44 ሺህ በላይ ሬዲዮ ጣቢያዎች በየእለቱ መረጃዎችን ለዓለም ህዝብ ያደርሳሉ
ከ5 በሊየን በላይ የሚሆኑ የዓለማችን ህዝቦች የራዲዮ አድማጮች መሆናቸውንም መረጃዎች ይጠቁማሉ
የራዲዮ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ11ኛ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው
ምንም እንኳ የኢንተርኔቱ ዓለም በመደበኛ የመገናኛ ብዙሃን ዘዴዎች ላይ የራሱ የሆነ ጫና ቢያሳድርም ራዲዮ ግን አሁንም ኃያልነቱን እና ጉልበተኝነቱን አላጣም።
በጣም ተዓማ የመረጃ ምንጭ ከሆኑት ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ራዲዮ፤ ለዓለማችን ህዝቦች ዋነኛ የመረጃ ምንጭ ከሆኑት ውስጥ አሁንም ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደተሰለፈ ቀጥሏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዓመታት በፊት ባጣው መረጃ መሰረት በዓለም ዙሪያ ከ44 ሺህ በላይ የራዲዮ ጣያዎች እንዳሉ ጠቁሟል።
በኢነዚህ የራዲዮ ጣቢያዎች አማካኝነትም በዓለም ዙሪያ ያሉ ከ5 ቢሊየን በላይ ሰዎች ማለትም ከዓለም ህዝብ ከ70 በመቶ በላይ በየእለቱ ከራዲዮን እንደሚያዳምጡም ነው መረጃው የሚጠቅመው።
ከ100 ዓመታት በላይ የመደመጥ ታሪክ ያለው ራዲዮ ሰዎች በየእለቱ በስራ ቦታቸው፣ በትራንፖርት ላይ እንዲሁም በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው ያደምጡታል።
ይህም ራዲዮ በዚህ የኢንተርኔት ዘመንም ኃያልነቱን ሳያጣ እንንቆይ ካደረጉት ውሰጥ አንዱ እንደሆነ ይነገራል።
ራዲዮ በኢትዮጵያ
ራዲዮና ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ጥብቅ ቁርኝት አላቸው። ያኔ ቴክኖሎጂው ባልደረሰብት እና እንዲህ እንደ አሁኑ መረጃ እንደልብ በማይገኝበት ጊዜ ሬዲዮ ብዙ ሰርቷል፡፡ የያኔው የኢትዮጵያ ሬዲዮ የአሁኑ ኢቢሲ ቀዳሚውን ሚና ተጫውቷል፡፡ሬዲዮን በማስተዋወቅም ረገድ ፈር ቀዳጅ ነው፡፡
በቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ “መልካም ፈቃድ” በ1920ዎቹ መጨረሻ ስራ የጀመረው የኢትዮጵያ ሬዲዮ መረጃ በቀላሉ ሊገኝ በማይችልበት በዛን ጊዜ ብቸኛ አማራጭ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ላለፉት 86 ገደማ አመታትም የብዙሃኑን ኢትዮጵያዊ ቀልብ ለመግዛት፤ከብዙሃኑም ልብ ውስጥ ለመቀመጥ የቻሉ ስራዎችን እየሰራም ከዛሬ ደጃፍ ደርሷል።
የኢትዮጵያ ሬዲዮን ፈለግ በመከተልም ብዙ የሬዲዮ ጣቢያዎችም ተመስርተዋል። አሁን ላይ ከ60 በላይ የተለያዩ ቋንቋዎች በአጭር፣መካከለኛ እና ረጅም እንዲሁም በኤፍ.ኤም ሞገዶች የሚያሰራጩ ከ75 በላይ የራዲዮ ጣቢያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በኢትዮጵያ ያለው የሬዲዮ ቁጥር ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እየተበራከተ መጥቷል። በአሁኑ ሰዓት በሃገሪቱ በተለይም በከተሞች ከሚገኙ የራዲዮ ጣቢያዎች መካከልም አብዛኞቹ የኤፍ.ኤም ጣቢያዎች ናቸው። የመጀመሪያው ኤፍ.ኤም የሬዲዮ ጣቢያ ኤፍ.ኤም 97.1 ነው፡፡ የመጀመሪያው የግል የሬዲዮ ጣቢያ ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 ነው።
ከ2003 ዓ/ም ጀምሮ ራሱን በኮርፖሬትነት በአዲስ መልክ ያደራጀው ሬዲዮ ፋናም ከኤፍ.ኤም 98.1 በተጨማሪ በርካታ ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ያሉት ቀዳሚ የሃገሪቱ የሚዲያ ተቋም ነው።
ዓለም አቀፍ የራዲዮ ቀን ዘንድሮ “ራዲዮ እና ተዓማኒነት” በሚል መሪ ሃሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ11ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ በመከበር ላይ ይገኛል።
የዓለም ራዲዮ ቀን እንዲከበር በስፔን የራዲዮ አካዳሚ አነሳሽነት ጥያቄው በፈረንጆቹ በ2010 ለዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (UNESCO) የስራ አመራር ከቀረበ በኋላ የተባበሩት መንግስታት ጉዳዩን ተቀብሎ ዓለም አቀፍ የራዲ ቀን በየዓመቱ የካቲት 6 እንዲከበር ወስኗል።
በመሆኑም የመጀመሪያው የራዲዮ ቀን የካቲት 6/2004 ዓ ም የተከበረ ሲሆን ዛሬ ለ11ኛ ጊዜ “ራዲዮ እና ተዓማኒነት” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው።