የሬዲዮ ቀን በአለም ደረጃ እንዲከበር ስፔን እንዴት ምክንያት ሆነች?
የሬዲዮ ቀን በአለም ደረጃ እንዲከበር ስፔን እንዴት ምክንያት ሆነች?
ሬዲዮ ኃያልና እጅግ ጉልበታምም ነው፡፡ጋራ ሸንተረርነት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና ቅርጽ ሳይገድበው መላው ዓለምን የሚያዳርስ ሞገድ አለው፡፡
በቀላሉ ሊያገኙት ከሚችሉ አድማጮች ጆሮ እየደረሰ፣ለእዝነ ልቦና እየቀረበ በዓይነ ህሊና እየተስተዋለ እያዝናና፣እያስተማረ፣እያሳወቀም ጭምር ከአንድ ምዕት ዓመት በላይ አስቆጥሮ እነሆ ከዛሬ ደጃፍ ደርሷል፡፡
ሬዲዮ ማህበረሰባዊ ግንዛቤን በመፍጠርና በማሳወቅ በሌሎችም መንገዶች ላበረከተውና በማበርከት ላይ ላለው ውለታ እውቅና ለመስጠትም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) አስተባባሪነት የዓለም ራዲዮ ቀን ዛሬ የካቲት 5 ቀን በመላው ዓለም ተከብሮ ውሏል፡፡
የቀኑ የመከበር መነሻዎች
የስፔን ሬዲዮ አካዳሚ ነው ለዓለም የሬዲዮ ቀን መከበር መሰረቱ፡፡ በወቅቱ ለነበረው የሃገሪቱ መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረትም ስፔን እ.ኤ.አ መስከረም 20፣2010 ዓ/ም የሬዲዮን ውለታ ሊያስታውስ የሚችል ቀን እንዲሰየምና እንዲከበር የዩኔስኮን ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ጠየቀች፡፡
ነገሩ ከሚመለከታቸው የሚዲያ አካላትና ሌሎችም ባለድርሻዎች ጋር በጥያቄው ላይ የመከረው ስራ አስፈጻሚ ቦርዱም ”ይከበር“ የሚል አብላጫ ድጋፍን በማግኘቱ ሃሳቡ ውሳኔን ያገኝ ዘንድ ጥያቄው በቀረበ በዓመቱ (2011) ለተሰበሰበው የድርጅቱ 36ኛ ጠቅላላ ጉባዔ አቀረበ፡፡ ጉባዔውም ሃሳቡን በመደገፍ ድርጅቱ በተመሰረተበት ዕለት በየዓመቱ የካቲት 13 (እ.ኤ.አ) እንዲከበር ወሰነ፡፡
ከ2011 ጀምሮም አባል ሃገራቱ በተለያዩ መንገዶች ቀኑን ያከብሩታል፤ስለ ሬዲዮ አበርክቶና አበርክቶው ሊያድግ ስለሚችልበት ሁኔታም ይመክሩበታል፡፡ዘንድሮም ለ9ኛ ጊዜ “ሬዲዮና ብዝሃነት” በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ውሏል፡፡
ኢትዮጵያም ለመጀመሪያ ጊዜ በዓሉን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) አጋፋሪነት የሃገሪቱን የብሮድካስት ባለስልጣናት፣አንጋፋ ጋዜጠኞችን እና ምሁራንን አሰባስባ አክብራለች፡፡
የራዲዮ አጀማመርና እድገት በኢትዮጵያ
ሬዲዮና ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ጥብቅ ቁርኝት አላቸው፡፡ያኔ ቴክኖሎጂው ባልደረሰብት እና እንዲህ እንደ አሁኑ መረጃ እንደልብ በማይገኝበት ጊዜ ሬዲዮ ብዙ ሰርቷል፡፡ብዙን አንቅቷል፤አስተምሯል፤አሳውቋል፤ አዝናንቷልም፡፡በተለይ ከከተሞች ርቆ ወደሚኖረው ኢትዮጵያዊ ጓዳ በመዝለቅ ረገድ ሬዲዮ የሚስተካከለው አልነበረም፡፡ ለዚህም ቀኑን ለመዘከርና ለማስታወስ የሚያስችለውን መድረክ ያጋፈረው የያኔው የኢትዮጵያ ሬዲዮ የአሁኑ ኢቢሲ ቀዳሚውን ሚና ተጫውቷል፡፡ሬዲዮን በማስተዋወቅም ረገድ ፈር ቀዳጅ ነው፡፡
በቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ “መልካም ፈቃድ” በ1920ዎቹ መጨረሻ ስራ የጀመረው የኢትዮጵያ ሬዲዮ መረጃ በቀላሉ ሊገኝ በማይችልበት በዛን ጊዜ ብቸኛ አማራጭ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ላለፉት 85 ገደማ አመታትም የብዙሃኑን ኢትዮጵያዊ ቀልብ ለመግዛት፤ከብዙሃኑም ልብ ውስጥ ለመቀመጥ የቻሉ ስራዎችን እየሰራም ከዛሬ ደጃፍ ደርሷል፡፡ ብዙዎችን ከአዳዲስ እውቀትና መረጃዎች ለማስተዋወቅና ብዙዎችን ለማስተማር፤ለማዝናናትም የቻሉ ስመጥር ጋዜጠኞችም ከዚሁ ተቋም ተገኝተዋል፡፡እነዚህ ጋዜጠኞችም ሊተኳቸው የሚችሉ ወጣት የሙያውን ባለቤቶች አፍርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ስርጭት (በ1956 ዓ/ም) ከመጀመሯ 30 አመታት ገደማ በፊት የመሰረተችው ይህ አንጋፋ የሬዲዮ ተቋም ዘመን ቀመስ በሆኑ የሃገሪቱ የለውጥ ሂደቶች የጎላ አበርክቶ አለው፡፡ አዳዲስ ርዕዮተ ዓለማዊ እና ሌሎች ጉዳዮችን የተመለከቱ ግንዛቤዎችን የመፍጠሩ ጉዞ ኢትዮጵያን ብሎም ለነጻነት ይታገሉ የነበሩ የአፍሪካ ሃገራትን እስከመደገፍ ይደርስ እንደነበርም ይነገራል፡፡
የኢትዮጵያ ሬዲዮን ፈለግ በመከተልም ብዙ የሬዲዮ ጣቢያዎችም ተመስርተዋል፡፡አሁን ላይ 62 በሚደርሱ የተለያዩ ቋንቋዎች በአጭር፣መካከለኛ እና ረጅም እንዲሁም በኤፍ.ኤም ሞገዶች የሚያሰራጩ 72 የራዲዮ ጣቢያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙም በዛሬው ክብረ በዓል ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ከነዚህም ውስጥ 50ዎቹ የማህበረሰብ፤13 ቱ ደግሞ የንግድ ሬዲዮ ጣቢያዎች ናቸው፡፡ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎቹ በዋናነት በተለያዩ የሃገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የሬዲዮ ቁጥር ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እየተበራከተ መጥቷል፡፡ በተለይ የኤፍ.ኤም ራዲዮ ጣቢያዎች ቁጥር ጨምሯል፡፡በአሁኑ ሰዓት በሃገሪቱ በተለይም በከተሞች ከሚገኙ የራዲዮ ጣቢያዎች መካከልም አብዛኞቹ የኤፍ.ኤም ጣቢያዎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ኤፍ.ኤም የሬዲዮ ጣቢያ ኤፍ.ኤም 97.1 ነው፡፡ የመጀመሪያው የግል የሬዲዮ ጣቢያ ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 ነው፡፡
ከ2003 ዓ/ም ጀምሮ ራሱን በኮርፖሬትነት በአዲስ መልክ ያደራጀው ሬዲዮ ፋናም ከኤፍ.ኤም 98.1 በተጨማሪ በርካታ ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ያሉት ቀዳሚ የሃገሪቱ የሚዲያ ተቋም ነው፡፡
የቀኑ የመከበር ፋይዳዎች
ሬዲዮ መስማት መቻልን እንጂ መማርን፣መጻፍ ማንበብን አይፈልግም፡፡ ፍላጎቱ ያለው ወቅታዊና አዳዲስ መረጃዎችን በዜና፣በፕሮግራም እና በሌሎችም የዘገባ መልኮች ለማድመጥ የሚፈልግ ሁሉ ባለበት እና የራዲዮ ሞገድ ሊደርስ በሚችልበት ቦታ ሆኖ እየሰራ፣እየተጓዘ አልያም ሌሎችንም እንቅስቃሴዎች እያደረገ ለማድመጥ ይችላል፡፡ ቀለል ባለ ወጪ ብዙሃኑን የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ በማድረግም ሬዲዮን የሚስተካከል የብሮድካስት ብዙሃን መገናኛ ዘዴ ዓይነት የለም፡፡
የዓለም የሬዲዮ ቀን ሲከበርም እነዚህን የሬዲዮ መልካም ነገር ግን ኃያል አጋጣሚዎች ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ዩኔስኮ የማህበረሰቡን ብዝሃነት በሚያጠናክር እና ለሁሉም ድምጽ በሚሆን መልኩ እንዲከበርም ያሳስባል፡፡ በተለይ ሃሰተኛና የፈጠራ ስራዎች በሚበዙበት በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን በቀላሉ ከብዙሃኑ ዘንድ ለመድረስ የሚችሉ የሬዲዮ መረጃዎች የማህረሰብን አንድነትና አብሮነት በማስጠበቅ፤በፈጠራ ወሬዎች ከመወሰድ በመታደግ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ድንቁም ለዚሁ ጉዳይ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ ሬዲዮ ዴሞክራሲን በማንበርና በማስረጽ ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ጥላቻና መለያየትን መታገል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡