ስደተኞች በአንድ ቢሰባሰቡ 14ኛዋን ባለብዙ ህዝብ ሀገር ይመሰርታሉ - ተመድ
በመላው አለም ከቀያቸው በሃይል የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 110 ሚሊየን መድረሱን የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን ገልጿል
የአለም የስደተኞች ቀን በየአመቱ ሰኔ 20 ታስቦ ይውላል
የመንግስታቱ ድርጅት ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ የሚገኙ ስደተኞችን ለመጠበቅ በፈረንጆቹ 1951 የስደተኞች ኮንቬንሽን አውጥቷል።
በ1967 ደግሞ በአለማቀፍ ደረጃ የሚገኙ ስደተኞችን ለመድረስ የሚያስችል አለማቀፍ ህግ መተዋወቁ የሚታወስ ነው።
ኮንቬንሽኑ ሲወጣ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን የነበረው የስደተኞች ቁጥር በ2011 15 ሚሊየን ፤ በ2022 መጨረሻ ደግሞ 35 ነጥብ 3 ሚሊየን ደርሷል።
አሃዙ በ2021 ከተመዘገበው በ8 ሚሊየን እንደሚልቅ ነው የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ያስታወቀው።
ከጠቅላላው ስደተኛ ውስጥ ከግማሽ በላዩ ከሶሪያ (6.5 ሚሊየን)፣ ዩክሬን (5 ነጥብ 7 ሚሊየን) እና አፍጋኒስታን (5 ነጥብ 7 ሚሊየን) ወጥተው በተለያዩ ሀገራት የተበተኑ ናቸው።
ጦርነት እና ግጭትን ሸሽተው በስደት ላይ የሚገኙ ሰዎችን በተመለከተ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሰኔ 20 በየአመቱ የአለም የስደተኞች ቀን ሆኖ ይከበራል።
በዚህ አመትም የስደተኞች ቀን ሲከበር በተለይ በዩክሬን እና ሱዳን ጦርነቶች የተፈናቀሉ ሰዎችን ማሰብ እንደሚገባ የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዴ አሳስበዋል።
ቱርክ 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ፤ ኢራን 3 ነጥብ 4 ሚሊየን እንዲሁም ዮርዳኖስ 3 ሚሊየን ስደተኞችን በማስጠለል ቀዳሚዎቹ ስደተኛ ተቀባይ ሀገራት ናቸው።
በአለም አቀፍ ደረጃ አስቸኳይ ድጋፍ ከሚፈልጉ ስደተኞች ውስጥ 76 በመቶው አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ ነው የሚገኙት፤ 70 ከመቶው ስደተኛ በጎረቤት ሀገራት ተጠልሏል።
“ይህም ስደተኞች ወደ ሀብታም ሀገራት እንደሚጓዙ የሚነዛውን የተሳሳተ መረጃ ያሳያል፤ እንደውም በተቃራኒው ነው” ብለዋል ፍሊፖ ግራንዴ።
እንደ መንግስታቱ ድርጅት መረጃ በአለማቀፍ ደረጃ ከ110 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።
ስደተኞች በአንድ ላይ ቢሰባሰቡ 14ኛዋን የአለማችን ባለብዙ ህዝብ ሀገር መመስረት ይችላሉ ተብሏል።