ታዋቂው የቻይና ቢሊየነር ጃክ ማ ከሁለት ዓመት ስደት በኋላ ወደ ሀገሩ ተመለሰ
የአሊባባ ኩባንያ መስራች ቻክ ማ በስደት ከሚኖርበት ጃፓን ወደ ቤጂንግ ተመልሷል
ቢሊየነሩ ከሀገሩ የተሰደደው የቻይና መንግስት ቁጥጥር አሰልቺ ነው በሚል ነበር
ታዋቂው የቻይና ቢሊየነር ጃክ ማ ከሁለት ዓመት ስደት በኋላ ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡
የቻይና እና የዓለማችን ቢሊየነር የሖነው ቻክ ማ ከሁለት ዓመት በፊት ነበር ሀገሩ ቻይናን ጥሎ መሰደዱ የተገለጸው፡፡
ለቢሊየነሩ መሰደድ ዋነኛ ምክንያት ነው የተባለው የቻይና መንግስት ጥብቅ ቁጥጥር እንደሆነ ሮይትርስ ዘግቧል፡፡
ዘገባው አክሎም ቻይና የኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር የዘረጋችው የዜሮ ኮቪድ ፖሊሲ ጃክ ማ እና ኩባንያዎቼ እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው መስራት ባለመቻላቸው ጃክ ማ የተሸለ ነጻነት ወዳለባት ጃፓን መሰደዱ ተገልጿል፡፡
የጃክ ማ መሰደድ የብዙዎችን ቻይናዊያንን ትኩረት የሳበ ሲሆን ብዙዎችም የፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ መንግስትን ተችተዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ሌሎች ባለሃብቶችም በቻይና መንግስት ጥብቅ ቁጥጥር ምቾት ነስቷል የተባለ ሲሆን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ጃክ ማ ወደ ሀገሩ እንዲመለስ በተደጋጋሚ እንደጠየቁት በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የቻይና ቁጥር አንድ ቢሊየነር ጃክ ማ ባሳለፍነው ሳምንት ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ ሀገሩ እንደተመለሰ የተለያዩ ዘገባዎች በፊት ገጻቸው ይዘው ወጥተዋል፡፡
የጃክ ማ ወደ ሀገሩ መመለስ ብዙ ቻይናዊያንን እንዳስደሰተ ከማህበራዊ የትስስር ገጾች የተጋሩ ሀሳቦችን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ በዘገባው ላይ ጠቅሷል፡፡
ይሁንና ጃክ ማ ወደ ቻይና መመለሱ ቢገለጽም ተመልሶ ወደ ጃፓን ስለማቅናቱ አልያም በቻይና ስራውን ስለመቀጠሉ እንዳልታወቀ ተገልጿል፡፡
ጃክ ማ አሁን ላይ 34 ቢሊዮን ዶላር ሀብት በመያዝ ከቻይና አምስተኛው ባለሃብት ሲሆን ከዓለም ደግሞ በ34ኛው የዓለማችን ባለጸጋው ሰው ናቸው፡፡