ለሥነ -ፈለክ ዘርፍ ጨዋታ ቀያሪ ይሆናል የተባለው የአለማችን ትልቁ ዲጂታል ካሜራ በሚቀጥለው አመት ስራ ይጀምራል
ካሜራው ከዚህ በፊት አይተናቸው የማናውቃቸውን 17 ቢሊዮን ኮከቦች እና 20 ቢሊዮን ጋላክሲዎች ማሳየት የሚችል ነው
ከ2015 ጀምሮ ግንባታ ላይ የነበረው ካሜራ በአሜሪካ መንግስት እና በግል በለሀብቶች የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ነው
በሰሜናዊ ቺሊ በሚገኝ ተራራ ጫፍ ላይ የተተከለው የዓለማችን ትልቁ ዲጂታል ካሜራ ወደ ስራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ነው።
ካሜራው ሙሉውን የሌሊት ሰማይ በከፍተኛ የዝርዝር ሁኔታዎች ፎቶግራፍ ማንሳት እና አንዳንድ ጥልቅ የአጽናፈ ዓለሙን (ዩኒቨርስ) ሚስጥሮችን ለመክፈት ያስችላል ተብሏል፡፡
በቬራ ሲ ሩብን ኦብዘርቫቶሪ ተቋም የተሰራው ካሜራ ከቺሊ ዋና ከተማ ሳንቲያጎ በስተሰሜን 482 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው 2682 ሜትር ከፍታ ባለው ተራራ ላይ የተተከለ ነው፡፡
3,200 ሜጋፒክስል ጥራት ሲኖረው ከ300 ሞባይል ስልኮች ጋር ተመሳሳይ የሆነ የፒክሴል መጠን ያለው ነው ተብሏል፡፡
በየሶስት ምሽቶቹ አጉሊ መነጸሩ የሚታየውን ሰማይ ምስል የሚያነሳ ሲሆን ይህም በሺህ የሚቆጠሩ ምስሎችን በማዘጋጀት የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች የሚንቀሳቀስ ወይም ብርሀኑን የሚቀይር ማንኛውንም ነገር እንዲያዩ ያስችላቸዋል።
በዚህ መሰረትም ከዚህ በፊት አይተናቸው የማናውቃቸውን ወደ 17 ቢሊዮን የሚጠጉ ኮከቦች እና 20 ቢሊዮን ጋላክሲዎችን ማሳየት የሚችል ስለመሆኑ ሲኤንኤን አስነብቧል፡፡
የስነ ፈለክ ተመራማሪ እና ካሜራውን ከሰሩ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት ክሌር ሂግስ ሩብን የተሰኝ መጠሪያ የተሰጠው ካሜራ ምህዋርን ከዚህ በፊት አይተነው በማናውቀው መንገድ እንድንመረምር ከማድረጉም በላይ እስከዛሬ ለመጠየቅ እንኳን ድፍረት ያጣንባቸውን ጥያቄዎችን እንድንመልስ የሚያስችል አቅም የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
ካሜራው በየምሽቱ 1000 ፎቶዎችን በማንሳት ለአስር አመታት ያህል የምሽት ሰማይን የሚቃኝ ሲሆን በነዚህ አመታት ውስጥም ስለ አዳዲስ የሳይንስ ዘርፎች፣ ስለ ጸሀይ ስርአት ፣ አስትሮይድ እና ስለ ህዋ አዲስ ክፍሎች ግኝቶችን ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝ ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡
ከ2015 ጀምሮ በግንባታ ላይ የሚገኝው ካሜራ ስለዳርክ ማተር መኖር ማረጋገጫ በሰጠችው እ.ኤ.አ በ 2016 በሞተችው አሜሪካዊቷ የስነ ፈለክ ተመራማሪ ቬራ ሩቢን የተሰየመ ነው፡፡
ይህ ፕሮጀክት ከ2000ዎቹ መጀመርያ አንስቶ በቢሊየነሮቹ ቻርልስ ሲሞኒ እና ቢልጌትስ ሲደገፍ የቆየ ሲሆን በኋላም በአሜሪካ ኢነርጂ እና ሳይንስ ፋውንዴሽን የጋራ ድጋፍ ቀጥሏል፡፡
የሩብን ዋነኛ ተልዕኮ የጊዜ እና የቦታ ዳሰሳ (ኤልኤስኤስ) ተብሎ ይጠራል፤ ካሜራው በየ 30 ሰከንድ ፎቶግራፍ ማንሳት ይችላል ይህም በየ 24 ሰዓቱ 20 ቴራባይት መረጃ ይሰበስባል እንደማለት ነው፡፡
ሆኖም እያንዳንዱን ምስል ከቺሊ ወደ ካሊፎርኒያ ወደ ሚገኝው የህዋ ምርምር ተቋም ለመላክ የሚወስደው ጊዜ 60 ሰከንድ ብቻ ነው፡፡
ምስሉን የሚቀበሉት ለዚህ ተብለው የተዘጋጁት ሰው ሰራሽ አስተውሎቶች ምስሉን በመተንተን ለየት ያለ ነገር ሲኖር ለብቻው በማስቀመጥ ተጨማሪ ምርምር እንዲደረግበት ጥቆማ ይሰጣሉ፡፡