ቱርክ በሶማሊያ የሚሳኤል እና የጠፈር ሮኬት መሞከርያ ጣቢያ ልትገነባ ነው
ሶማሊያ በአፍሪካ ምስራቃዊ ጫፍ ላይ ያላት ስልታዊ አቀማመጥ በህንድ ውቅያኖስ ላይ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን ለመተኮስ ምቹ ያደርጋታል ተብሏል
ቱርክ አለም አቀፉን የጠፈር ፉክክር ለመቀላቀል ለአመታት ስትዘጋጅ ቆይታለች
ቱርክ በሶማሊያ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎች እና የጠፈር ሮኬቶች መሞከርያ ጣብያ ለመገንባት ከሞቃዲሾ መንግሰት ጋር እየተነጋገረች መሆኑ ተነግሯል፡፡
አንካራ የባላስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ ህንድ ውቅያኖስ በማስወንጨፍ ሙከራዎችን ለማድረግ ሶማሊያ በአፍሪካ ቀንድ ጫፍ ያላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ወሳኝ ሆኖ ተገኝቷል ያሉት ብሉምበርግ ያነጋገራቸው ምንጮች ተናግረዋል፡፡
በስም ያልተጠቀሱት ምንጮች እንደገለጹት ውይይቱ ሲጠናቀቅ ቱርክ በሶማሊያ የሙከራ ጣብያዎችን ለመገንባት ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች፡፡
በተጨማሪም ሶማሊያ ከምድር ወገብ ጋር ያላት ቅርበት የጠፈር ጣብያዎችን ለመገንባት እና ከምድር ወግብ የሚነሱ የጠፈር ሮኬቶችን ፍጥነት እና ቅልጥፍና እንደሚጨምረው ተነግሯል፡፡
አሜሪካ ፣ ሩስያ ፣ ቻይና እና ህንድ በዋናነት ከፍተኛ ፉክክር እያደረጉበት የሚገኝውን የአለም አቀፉን የጠፈር ፉክክር ለመቀላቀል ቱርክ ባለፉት አመታት የተለያዩ ዝግጅቶችን ስታደርግ እንደነበር ዘገባው ጠቅሷል፡፡
የሶማሊያ መንግስት ጥያቄውን ተቀብሎ ፈቃድ የሚሰጥ ከሆነ ሀገሪቱ ወደ ጠፈር ሮኬቶችን ለማስወንጨፍ ያላትን እቅድ አንድ እርምጃ ወደ ፊት የሚወስደው ነው፡፡
ብሉምበርግ ስለጉዳዩ የቱርክ መከላከያ ሚንስቴር እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ብሄራዊ ደህንነት አማካሪን ለማነጋገር ሞክሩ ሀሳብ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳየሆኑ ቀርተዋል፡፡
በ2022 የቱርክ ፕሬዝደንት ረሲብ ጣይብ ኢርዶጋን በሀገር ውስጥ የሚመረት ታይፉን የተባለ 560 ኪሎሜትር የሚጓዝ የመካከለኛ ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል አስተዋውቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከዚህ ጊዜ በኋላ ሀገሪቷ የረጀም ርቀት ሚሳኤሎችን ለማምረት እና ለመሞከር ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራትም በሙከራዎች አለመሳካት ሊፈጠሩ የሚችሉ ፍንዳታዎች ወደ መኖርያ አካባቢዎች እና ጎረቤት ሀገራት በመስፋፋት ጉዳት እንዳያደርሱ በመስጋት እንዲዘገይ ተደርጎ ቆይቷል፡፡
በቅርብ አመታት ከሶማሊያ መንግስት ጋር ጠናካራ ግንኙነት ለመመስረት ጥረት እያደረገች የምትገኝው አንካራ ትምህርት ቤቶችን እና መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ለሞቃዲሾ አጋርነቷን እያሳየች ትገኛለች፡፡
ከዚህ ባለፈም ሀገራቱ በተፈራረሙት የመከላከያ ትብብር ስምምነት የሶማሊያን የባህር ዳርቻዎች ለመጠበቅ መርከቦቿን አሰማርታለች፡፡