ሁለት ጠባብ ክፍሎች ያሏት የአለማችን ትንሿ እስርቤት
በፈረንጆቹ 1856 የተገነባችው እስርቤት በበጀት እጥረት ምክንያት ማስፋፊያ ሳይደረግላት አሁንም ድረስ አገልግሎት እየሰጠች ነው
በሳርክ ደሴት የምትገኘው እስርቤት በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ሰፍራለች
በእንግሊዝና ፈረንሳይ መካከል የምትገኘው ሳርክ ደሴት የአለማችን ጠባቡ እስርቤት ይገኝባታል።
5 ኪሎሜትር ርዝመትና 1 ነጥብ 6 ኪሎሜትር ስፋት ያላት ጠባብ ደሴት መኪናም ሆነ አስፋልት መንገድ የላትም።
600 የማይሞላ ህዝብ በሚኖርባት ደሴት እስርቤት በመገንባት ግን ከቀዳሚዎቹ ተርታ ትሰለፋለች።
በፈረንጆቹ 1856 የተሰራችው ጠባብ እስርቤት አሁንም ድረስ ማገልገሏን መቀጠሏን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።
እስርቤቷ ሁለት ክፍል ያላት ሲሆን፥ ስፋታቸው አራት ካሬ እንኳን አይሞላም።
በውስጣቸው አነስተኛ የእንጨት አልጋ ብቻ የሚገኝባቸው ክፍሎች ውስጥ የሚታሰሩ ሰዎች ለሁለት ቀናት ብቻ ነው የሚቆዩት።
መስኮት በሌላቸው ጠባብ ክፍሎች ለሁለት ቀናት የቆዩ ታራሚዎች ወደ ሳርክ ጎረቤት ጉርነሲ ደሴት ትልቅ ማረሚያ ቤት ይዘዋወራሉ ተብሏል።
በ1832 በሳርክ ደሴት እስርቤት ለመገንባት ሲታቀድ ባለሁለት ጠባብ ክፍሎቹን ለመስራት አልነበረም የሚለው የጉርነሲ ደሴት ድረገጽ በወቅቱ የገጠመው የበጀት እጥረት የአለማችን ጠባቧ እስርቤት እንድትገነባ ማድረጉን አውስቷል።
አስደናቂው ነገር እስርቤቷ ባለፉት 168 አመታት አገልግሎት እየሰጠች መቀጠሏ ነው።
የአለም ድንቃድንቅ መዝገብም በሳርክ ደሴት የምትገኘውን ባለሁለት ክፍል እስርቤት “የአለማችን ጠባቧ እስርቤት” ብሎ መዝግቧታል።