ባንግላዲሽ በማረሚያ ቤት ውስጥ 26 እስረኞችን አንቆ የገደለውን ታሳሪ ፈታች
ከእስር የተለቀቀው ግለሰብ በማረሚያ ቤት መልካም ስነ ምግባር አሳይቷል በሚል ነው
ሻህጃሃን ቢያን የተሰኘው ታራሚ በግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ የ42 ዓመት እስር ተፈርዶበት ነበር
ባንግላዲሽ በማረሚያ ቤት ውስጥ 26 እስረኞችን አንቆ የገደለውን ታሳሪ ፈታች።
በእስያዊቷ ባንግላዲሽ መዲና ዳካ ከተማ ባለ እስር ቤት የ42 ዓመት ፍርደኛ የነበረ ታራሚ ከእስር መፈታቱ ብዙዎችን አስገርሟል።
ይህ የ42 ዓመት ፍርደኛ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ 26 ታራሚዎችን አንቆ መግደሉ እና ታራሚው መልካም ስነ ምግባር አሳይቷል በሚል መፈታቱ በእስያ ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል፡።
ነገሩ እንዲህ ነው።
ባንግላዲሽ በተለያዩ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለው የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሰዎች ላይ ፍርዱን የምትፈጽመው አንቆ በመግደል ነው።
በሀገሪቱ መዲና ዳካ ከተማ ያለው የዳካ ማረሚያ ቤት ደግሞ ከባድ ወንጀሎችን የፈጸሙ ወንጀለኞችን ማረሚያ ስፍራ ነው።
ሻህጃሃን ቢያን የተሰኘው ታራሚ በግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ ነበር የ42 ዓመት እስር ተፈርዶበት ወደ ዳካ ማረሚያ ቤት የተዛወረው።
ከፈረንጆቹ 2001 ጀምሮም የሽብር እና ግድያ ወንጀል ፈጽመው ጥፋተኛ የተባሉ ፍርደኞች ወደ ዳካ ማረሚያ ቤት መዛወር ይጀምራሉ።
የ42 ዓመት እስር የተላለፈበት ሻህጃሃን በሞት ፍርድ የተላለፈባቸውን ሰዎች ፍርዱን ለመፈጸም እውቀቱ እንዳለው ለማረሚያ ቤቱ ሃላፊዎች ያስረዳል።
በዚህ መሰረትም ይህ ግለሰብ የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው ሰዎችን አንቆ እንዲገድል በማረሚያ ቤቱ ፈቃድ አግኝቷል ተብሏል።
ታራሚውም አንድ የሞት ፍርድ የተላለፈበትን ፍርደኛ አንቆ ሲገድል ከእስሩ ላይ የሁለት ወራት የእስር ወራት ጊዜ ሲቀነስለት እንደቆየም ተገልጿል።
በዚህ መሰረትም ታራሚው በማረሚያ ቤት ቆይታው 26 የሞት ፍርድ የተላለፈባቸውን ሰዎች አንቆ መግደሉ እና በተጨማሪነት መልካም ስነ ምግባር ማሳየቱን ተከትሎ ከእስር መለቀቁ ተሰምቷል።
ጉዳዩ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መሰማቱን ተከትሎ በባንግላዲሽ ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ የሆነ ሲሆን እንዴት ከእስር ይፈታል እና ቢፈታ ምን ችግር አለው የሚሉ ሀሳቦች በስፋት እየተንሸራሸሩ ነው ተብሏል።
ከእስር የተፈታው የቀድሞ ታራሚም “የሞት ፍርድ የተላለፈባቸውን ሰዎች እኔ አንቄ ባልገድላቸው በሌላ ሰው መገደላቸው አይቀርም ነበር” ሲል ተናግሯል።
በማረሚያ ቤት ጥሩ ጊዜ ነበረኝ ያለው የ74 ዓመቱ ሻህጃሃን ድርጊቱን የፈጸምኩት ታዝዤ እንጂ ፈልጌ አይደለም ሲልም አክሏል ሲል ለየት ያሉ ዘገባዎችን በማስነበብ የሚታወቀው ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።