10 የአለማችን ግዙፍና ውድ ፕሮጀክቶች
ከ100 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ ከሚደረግባቸው 10 የአለማችን ሜጋ ፕሮጀክቶች ውስጥ አራቱ በአረብ ሀገራት ይገኛሉ
በሳኡዲ፣ ኩዌት እና ማሌዥያ ግዙፍ ከተሞች ግንባታ እየተካሄደ ነው
ከአመታት በፊት አንድ ፕሮጀክት ሜጋ ወይም ትልቅ ነው ለመባል 10 ቢሊየን ዶላር እና ከዚያ በላይ ወጪ ሊደረግበት ይገባ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ግን ከ100 ቢሊየን ዶላር በላይ በጀት የተያዘላቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ናቸው።
21ኛው ክፍለዘመን ከመጠናቀቁ በፊትም 1 ትሪሊየን ዶላር የሚያወጣ ሜጋ ፕሮጀክት ሊኖር እንደሚችል የግንባታ ሶፍትዌር ኩባንያው 1ቢዩልድ ግምቱን አስቀምጧል።
ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ከ100 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ ከሚደረግባቸውና ግንባታቸው ከተጀመረ 10 ግዙፍ ፕሮጀክቶች ውስጥ አራቱ በባህረ ሰላጤው ሀገራት እንደሚገኙ ገልጿል።
በሰሜን ምዕራብ ሳኡዲ እየተገነባ ያለውና እስከ 2030 ድረስ 300 ሺህ ሰዎችን ማኖር ይችላል የተባለው የ”ኒዮም ከተማ” ፕሮጀክት 500 ቢሊየን ዶላር ወጪ ይደረግበታል።
በጂዳ እየተገነባ ያለው የንጉስ አብዱላህ የኢኮኖሚ ከተማ እና በሰሜን ኩዌት ግንባታው እየተካሄደ የሚገኘው የ”ሲልክ ከተማ”ም በአለማችን ከቀዳሚዎቹ ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
ስድስቱን የገልፍ ትብብር ምክርቤት አባል ሀገራትን (ሳኡዲ፣ ኤምሬትስ፣ ባህሬን፣ ኩዌት፣ ኦማን እና ኳታር) በባቡር መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ያለው ፕሮጀክት 250 ቢሊየን ዶላር ይጠይቃል።
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራትን በመንገድ፣ ባቡር፣ በአየር እና ውሃ ትራንስፖርት የሚያስተሳስረው “ቲኢኤን-ቲ የባቡር ኔትወርክ” ፕሮጀክት በ600 ቢሊየን ዶላር ቀዳሚው ነው።