ስፖርት
ክርስቲያኖ ሮናልዶ አዲስ ክብረወሰን በዩቲዩብ
በማህበራዊ ሚዲያዎች ከ917 ሚሊየን በላይ ተከታዮች ያሉት ሮናልዶ በዩቲዩብም አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቧል
የፖርቹጋላዊው ኮከብ የዩቲዩብ ቻናል በቀናት ውስጥ ከ51 ሚሊየን በላይ ተከታዮችን አግኝቷል
ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በእግርኳስ ሜዳ ሪከርዶችን የሰባበረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በማህበራዊ ሚዲያዎች የአለማችን ቀዳሚው ታዋቂ ሰው ነው።
ሮናልዶ በኤክስ(ትዊተር) 112.5 ሚሊየን፣ በፌስቡክ 170 ሚሊየን እንዲሁም በኢንስታግራም 636 ሚሊየን ተከታዮች አሉት።
በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ከ917 ሚሊየን በላይ ተከታዮች ማፍራት የቻለው የኣግርኳስ ፈርጥ ባለፈው ሳምንት በከፈተው የዩቲዩብ ገጽም ተጽዕኖ ፈጣሪነቱን አሳይቷል።
የ39 አመቱ የእግርኳስ ኮከብ የዩቲዩብ ገጹን ባስተዋወቀ በ90 ደቂቃዎች ውስጥ 1.69 ሚሊየን ተከታዮችን በማግኘት አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቧል።
ሮናልዶ በሰባት ቀናት ውስጥ 23 ቪዲዮዎችን የጫነበት የዩቲዩብ ገጹ ከ51 ሚሊየን በላይ ተከታዮችን አግኝቷል፤ በየደቂቃው የተከታዩ ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።
ይህም ፖርቹጋላዊው ተጫዋች ከተጫወተባቸው ክለቦች አጠቃላይ የዩቲዩብ ተከታይ ቁጥር የላቀ ሆኗል።