ቻይና በብር ሜዳልያዎች ብዛት በአሜሪካ ተበልጣ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች
ለ17 ቀናት በፓሪስ የተካሄደው 33ኛው ኦሎምፒክ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።
ከ206 ሀገራት ከ10 ሺህ በላይ አትሌቶች የተሳተፉበት የፓሪስ ኦሎምፒክ በአሜሪካ የበላይነት ተጠናቋል።
40 የወርቅ፣ 44 የብር እና 42 የነሃስ ሜዳልያዎችን ያገኘችው አሜሪካ ከቻይና ጋር በወርቅ ሜዳልያ እኩል ብትሆንም በብርና ሜዳልያዎች ብዛት በመብለጥ የፓሪስ ኦሎምፒክ የሜዳልያ ሰንጠረዥን በበላይነት አጠናቃለች።
አሜሪካ ካለፉት ሰባት ኦሎምፒኮች ስድስቱን በቀዳሚነት ማጠናቀቅ ችላለች።
በአቴንስ በፈረንጆቹ በ1896 ከተደረገው ኦሎምፒክ አንስቶ በተደረጉ የኦሎምፒክ ውድድሮች በ19ኙ አንደኛ ሆና በማጠናቀቅም ትልቅ ስኬት አስመዝግባለች።
የዘንድሮው ኦሎምፒያድ አዘጋጅ ፈረንሳይ ደግሞ ጃፓን እና አውስትራሊያን ተከትላ አምስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
32 አይነት ስፖርታዊ ውድድሮች በተካሄዱበት የፓሪስ ኦሎምፒክ 91 ሀገራት በሜዳልያ ሰንጠረዡ ውስጥ ገብተዋል።