ድርጅቱን በተተኪ ዋና ዳይሬክተርነት ለመምራት የሚፎካከሩ 8 እጩዎች ቀርበዋል
የቀድሞዋ የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት እየተወዳደሩ ነው
የዓለም የንግድ ድርጅት በዋና ዳይሬክተርነት የሚመራውን አካል ለማግኘት የሚያስችለውን የምርጫ ሂደት ጀመረ፡፡ ምርጫው የድርጅቱ ጠቅላላ ምክር ቤት በሚያስቀምጣቸው ሂደቶች የሚፈጸም ነው፡፡
ከሳምንት በፊት በተጠናቀቀው የእጩዎች ጥቆማ መሰረትም 8 እጩዎች ለውድድር ቀርበዋል፡፡ ከእጩዎቹ መካከል ኬንያዊቷ አምባሳደር አሚና መሃመድ (ዶ/ር) እና ናይጄሪያዊቷ ንጎዚ ኦኮንጆ (ዶ/ር) ይገኙበታል፡፡
አምባሳደር አሚና ከአሁን ቀደም ሃገራቸውን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡
አብደል ሃሚድ ማምዱህ የተሰኙ ግብጻዊም ከእጩዎቹ መካከል ይገኛሉ፡፡
የእንግሊዝ፣የኮሪያ፣የሳዑዲ አረቢያ እና የሜክሲኮ ተወካዮችም በእጩዎቹ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል፡፡
እጩዎቹ በቀጣዮቹ 3 ወራት ራሳቸውን ለአባል ሃገራቱ በማስተዋወቅ ሃላፊነቱን ለመረከብ የሚፎካከሩበት ይሆናል፡፡
እንደ ብሉምበርግ ጋዜጣ ዘገባ አምባሳደር አሚና ዓለም አቀፋዊውን ተቋም በዳይሬክተርነት ለመምራት የሚያስችላቸውን የአሸናፊነት ቅድመ ግምት አግኝተዋል፡፡
የወቅቱ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ሮቤርቶ አዝቬዶ በፈቃዳቸው ከሃላፊነት ለመልቀቅ መወሰናቸውን ተከትሎ ነው ተተኪያቸውን ለማግኘት የሚያስችለው ምርጫ የሚካሄደው፡፡
እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ ላለፉት ሰባት ዓመታት ድርጅቱን የመሩት አዝቬዶ ሁለተኛው የዳይሬክተርነት የስልጣን ዘመናቸው ከመጠናቀቁ አንድ አመት ቀደም ብለው በቀጣዩ ወር መጨረሻ በራሳቸው ፈቃድ ከሃላፊነት ለመልቀቅ መወሰናቸውን አስታውቀዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2017 ድርጅቱን ለተጨማሪ አራት አመታት እንዲመሩ ሃላፊነቱ ተሰጥቷቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ድርጅቱ የዓለምን 98 በመቶ የንግድ ድርሻ የሚይዙ 164 አባል ሃገራት አሉት፡፡ የአባልነት ጥያቄ ያቀረቡ 24 ሃገራትም ለጥያቄያቸው የሚሰጠውን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ ከነዚህ 24 ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡ አባል ለመሆን በሚያስችላት የዝግጅት ሂደት ላይ መሆኗም አይዘነጋም፡፡