ዣቪ በውድድር አመቱ መጨረሻ ከባርሴሎና ጋር እንደሚለያይ ይፋ አደረገ
ባርሴሎና ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሶስቱ መሸነፉን ተከትሎ ነው ስፔናዊው አሰልጣኝ በሰኔ ወር መጨረሻ ክለቡን እሰናበታለሁ ያለው
ዣቪ ሄርናንዴዝ በባርሴሎና ለ17 አመታት ተጫውቶ 25 ዋንጫዎችን ማንሳቱ ይታወሳል
የባርሴሎናው አሰልጣኝ ዣቪ ሄርናንዴዝ በውድድር አመቱ መጨረሻ ክለቡን ማሰልጠን ለማቆም መወሰኑን ገለጸ።
የቀድሞው የባርሴሎና እና የስፔን ብሄራዊ ቡድን አማካይ የኳታሩን አል ሳድ ለቆ የቀድሞ ክለቡን በአሰልጣኝነት የተረከበው በህዳር ወር 2021 እንደነበር ይታወሳል።
ባርሳን በ2022/23 የስፔን ላሊጋ ሻምፒዮን ማድረግ የቻለው አሰልጣኙ፥ ትናንት በሜዳው በቪያሪያል የደረሰበት ሽንፈት የአንድ አመት ኮንትራት እየቀረው ክለቡን ለመልቀቅ እንዲወስን ያደረገው ዋነኛው ምክንያት ነው ተብሏል።
ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በሶስቱ የተሸነፈው ባርሴሎና በላሊጋው በ44 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ቢቀመጥም ከመሪው ሪያል ማድሪድ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት 10 ደርሷል።
ባለፈው ጥር በስፔን ሱፐር ካፕ ፍጻሜ በተቀናቃኙ ሪያል ማድሪድ መሸነፉና በቅርቡም በኮፓዴላሬ ዋንጫ በአትሌቲኮ ቢልባዎ ተሸንፎ ከሩብ ፍጻሜ ውጭ መሆኑም በዣቪ ላይ ጫና ማብዛታቸው ተነግሯል።
“ለባርሳ ሁሉንም ነገሬን ሰጥቻለሁ፤ ክለቡን ማሰልጠን ከባድ ሃላፊነት ቢሆንም ሰዎች አይረዱህም” ያለው ዣቪ፥ በሰኔ ወር መጨረሻ ከባርሳ ከለቀቀ በኋላ ሌላ ክለብ ከማሰልጠን ይልቅ ከልጆቹ ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንደሚፈልግ አስታውቋል።
በትናንቱ የቪያሪያል የ5 ለ 3 ሽንፈት የተበሳጨው የ44 አመቱ አሰልጣኝ “ክለቡ ለውጥ ይፈልጋል፤ የመፍትሄው አካል እንጂ ችግር መሆን አልፈልግም” ብሏል።
ከባርሴሎና አሰልጣኝነት ለመልቀቅም ከፕሬዝዳንቱ ዮሃን ላፖርታ ጋር መምከሩንና መግባባት ላይ መድረሳቸውን ነው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የጠቆመው።
በባርሴሎና ለ17 አመታት የተጫወተው ዣቪ ሄርናንዴዝ ለክለቡ 767 ጊዜ ተሰልፎ ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል።
በቆይታውም አራት የሻምፒዮንስ ሊግ እና ስምንት የላሊጋ ዋንጫዎችን ጨምሮ 25 ዋንጫዎችን ማንሳት መቻሉን ሬውተርስ አስታውሷል።
ዣቪ ሄርናንዴዝ ስፔንን በ2010 በደቡብ አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የአለም ዋንጫ ሻምፒዮን ያደረገው ስብስብ አካል እንደነበርም አይዘነጋም።