ባርሴሎና በ2019 የተጫዋቾች ክፍያ ቀዳሚ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ
‘ግሎባል ስፖርት ሳላሪ’ የተሰኘው የጥናት ተቋም ባወጣው መረጃ ባርሴሎና በ2019 ለመጀመሪያ ቡድን ተጫዋቾች በአማካይ 12.28 ሚሊዮን ፓውንድ በመክፈል 1ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ያለፈውን ዓመት ደረጃውን አስጠብቋል፡፡
ክለቡ ባለፈው ዓመት የውድድር ዘመን በአማካይ 13.7 ሚሊዮን ፓውንድ ነበር ለመጀመሪያው ቡድን ተጫዋቾቹ የከፈለው፡፡
የክለቡን አማካይ ክፍያ በዋናነት ከፍ ያደረገው ደግሞ የ6 ጊዜ ባሎን ዶር አሸናፊው የሊዮኔል ሜሲ ዳጎስ ያለ ክፍያ ነው፡፡ ሜሲ በ 2018 ኮንትራቱ መሰረት በ2019 ከ65 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ተከፍሎታል፡፡ እንደ ፎርብስ መረጃ አጠቃላይ የዓመቱ ገቢው ደግሞ 182 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይሄም የአመቱ ከፍተኛ ገቢ ያገኘ ስፖርተኛ አድርጎታል፡፡
ሜሲን በመከተል በ175 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ 2ኛ ደረጃን የያዘው ደግሞ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ነው፡፡
ባርሴሎናን በመከተል በ2019 በሁለተኛነት ለተጫዋቾቹ በአማካይ ከፍተኛ ክፍያ የከፈለው ደግሞ በ11.1 ሚሊዮን ፓውንድ ሪያል ማድሪድ ነው፡፡ ጁቬንቲዩስ በ10.1 ሚሊዮን ፓውንድ ሦስተኛ ሆኗል፡፡
ጁቬ በ2017/18 የውድድር ዘመን 32ኛ ከነበረበት በቀጣዩ ዓመት 10ኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን በ2019 ደግሞ 3ኛ ደረጃ ላይ በፍጥነት መምጣቱ አስደናቂ እንደሆነ ነው የተዘገበው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ክለቡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሮናልዶን ጨምሮ ስመጥር ከዋክብትን በመሰብሰቡ ነው፡፡
በ‘ግሎባል ስፖርት ሳላሪ’ ጥናት መሰረት ለስፖርተኞቻቸው ከፍተኛ ክፍያ በመክፈል ከ4ኛ-11ኛ ያሉትን ደረጃዎች የያዙት የሰሜን አሜሪካ የቅርጫት ኳስ ክለቦች ናቸው፡፡
ከከፍተኛ 20 ከፍተኛ ከፋዮች ተርታ የተሰለፉ ሌሎች የእግርኳስ ክለቦች፣ በ12ኛነት የፈረንሳዩ ፒኤስጂ እና በ13ኛነት የእንግሊዙ ማንቺስተር ሲቲ ናቸው፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን