የሀውቲ ታጣቂዎች ሁለት ሚሳይሎች ወደ ማዕከላዊ እስራኤል ማስወንጨፋቸውን ገለጹ
እስራኤል እነዚህ ሚሳይሎች ኢላማቸውን ሳይመቱ ተመትተው ወድቀዋል ብላለች
የሀውቲ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው የፍልስጤሙ ሀማስ አጋርነት ለማሳየት በእስራኤል ላይ ለአንድ አመት ያህል ተከታታይ ጥቃት እየፈጸሙ ነው
በኢራን የሚደገፉት የሀውቲ ታጣቂዎች ሁለት ሚሳይሎችን በማዕከላዊ እስራኤል ወደምትገኘው የጃፋ ከተማ ማስወንጨፋቸውን በትናንትናው እለት ገልጸዋል።
እስራኤል እነዚህ ሚሳይሎች ኢላማቸውን ሳይመቱ ተመትተው ወድቀዋል ብላለች።
የእስራኤል ጦር እንደገለጸው የተተኮሰው 'ሰርፌስ ቱ ሰርፌስ' ሚሳይል በመላው ማዕከላዊ እስራኤል የማስጠንቀቂያ ደዎሎች እንዲደወሉ እና ነዋሪዎች ወደ መሸሸጊያ እንዲሮጡ አድርጓል ብሏል።
"በማዕከላዊ እስራኤል ደዎሎች ከተሰሙ በኋላ ከየመን የተተኮሰው ሚሳይል በተሳካ ሁኔታ" በእስራኤል የአየር ኃይል መክሸፉን ጦሩ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
መግለጫው ሚሳይሉን ማን እንዳስወነጨፈው ግልጽ አላደረገም።
ሀውቲዎች እንዳሉት ፍልስጤም2 የተባለው አንደኛው ሚሳይል ኢላማው ላይ ደርሷል። ሁለተኛ ሚሳይል ዱ አልፊቃር እንደሚባል የገለጹት ሀውቲዎች ውጤቱን አልገለጹም።
የየመኑ ቡድን ዘመቻው አላማውን ማሳካቱን እና በቻፋ እና ኢላት የነበሩ በርካታ ድሮኖችን ኢላማ ማድረጉን ጠቅሷል።
አብዛኛውን የየመን ክፍል የሚቆጣጠሩት እና በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት የሀውቲ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው የፍልስጤሙ ሀማስ አጋርነት ለማሳየት በእስራኤል ላይ ለአንድ አመት ያህል ተከታታይ ጥቃት እየፈጸሙ ነው።
እስራኤል ከጋዛው ጦርነት ጎን ለጎን ከሀውቲዎች እና በሰሜን በኩል በሊባኖስ ከሚንቀሳቀሰው ሄዝቦላ ጋር እየተዋጋች ትገኛለች።
እስራኤል በቅርቡ ትኩረቷን ወደ ሰሜን በማዞር የሄዝቦላ መሪዎችን ገድላለች፣ በሊባኖስ ላይ የእግረኛ ጦር ጥቃት ከፍለች።
ይህ ጦርነት የእስራኤል አጋር የሆነችውን አሜሪካን እና ኢራንን ወደ ጎትቶ ሊያስገባቸው ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።