በሶማሊያ ሰላም አሰከባሪ ያሰማሩ ሀገራት በግብጽ ወደ ቀጠናው መጠጋት ቅሬታቸውን እያሰሙ መሆኑ ተነገረ
በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ልዑክን (አትሚስ) በሚተካው ሀይል ግብጽ ልሳተፍ ማለቷ ላይ ጥያቄ ተነስቷል
የአውሮፓ ህብረት ከተመድ እና የአፍሪካ ህብረት ጋር አደረኩት ባለው ውይይት በግብጽ ተሳትፎ ዙርያ ተቃውሞ እንዳልሰማ ገልጿል
በሶማሊያ አዲስ በሚሰማራው የሰላም አስከባሪ ሀይል ውስጥ የግብጽን ተሳትፎ ጥያቄ እየተነሳበት መሆኑ ተነገረ፡፡
በላፉት አመታት በሶማሊያ በነበረው የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ልዑክ (አትሚስ) ውስጥ እየተሳተፉ ከሚገኙ ሀገራት መካከል የግብጽን ወደ ቀጠናው መቅረብ በጥርጣሬ የሚመለከቱ ሀገራት ተቃዎሟቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
በመጪው ጥር ወር የስራ ጊዜው የሚጠናቀቀውን (አትሚስ) የሚተካው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (AUSSOM) ውስጥ 5 ሺህ ጦር የማሰማራት ፍላጎት እንዳላት ካይሮ አስታውቃለች፡፡
ከዚህ ባለፈም 680 የፖሊስ አባላትን እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር በደረሰችው የሁለትዮሽ የመከላከያ ስምምነት ተጨማሪ የደህነንት እና ጸጥታ ስራዎችን የሚያከናውን 5 ሺህ ጦር ለመላክ እቅድ አላት፡፡
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሲማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የወደብ የመግባብያ ስምምነት ካልሰረዘች በአዲሱ ልዑክ ውስጥ መሳተፏን አልፈቅድም ያለቸው ሶማሊያ ከግብጽ ጋር ያላት ግንኙነት እያደገ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡
ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ በሶማሊያ በሚደረገው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ጉልህ ሚና ሲጫወቱ ከነበሩት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን ኬንያ ፣ ኡጋንዳ ፣ ብሩንዲ እና ጂቡቲ ሌሎች ጦር ያዋጡ ሀገራት ናቸው፡፡
ሀገራቱ የግብጽ ወደ አካባቢው መጠጋት ቀጠናውን አለመራጋጋት ሊያባብሰው እንደሚችል ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ እንደሚገኙ ዘ ኢስት አፍሪካን አስነብቧል፡፡
ኡጋንዳ ተቃዎሞቸውን ካሰሙ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ግብጽ እስከዛሬ የት ነበርች ሲሉ መጠየቃቸው ተዘግቧል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ልዑክ በሶማሊያ (አትሚስ) የሚተካው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (AUSSOM) በተግባር እንጂ በመዋቅር ደረጃ ከቀድሞው ተልዕኮ የሚለይ አይደለም ያሉት ሚንስትሩ የአዲስ ሀገር መካተት ያለውን ጠቀሜታ ምን እንደሆነ በጥያቄ መልክ አንስተዋል፡፡
ካይሮ በቀጠናው አሰማራዋለሁ ያለችው ጦር በአካባቢው በሚገኘው ጥምር ጦር ላይ በትጥቅ እና በሌሎች አሰላለፎች በአጠቃላይ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ስጋቶች እየተሰሙ ነው፡፡
በአለም አቀፍ ሰላም እና ደህንነት እንዲሁም ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ምርምሮችን የሚወጣው ኢንስቲትዩት ፎር ግሎባል ስተዲስ (አይጂኤስ) ግብጽ ያቀረበችው የአጋርነት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ በሶማሊያ ጦሯን የምታሰፍር ከሆነ የአካባቢውን ሁኔታ የሚለዋውጡ አዳዲስ ሁነቶች ሊከተሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል፡፡
ከእነዚህ መካከልም ይህ ውሳኔ ካይሮን በቀጠናው ግዙፍ የሶማሊያ ወታደራዊ አጋር ሲያደርጋት ሽብረተኝነትን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት እና የግብጽን መጠጋት በተመለከተ ተቃሞዋን እየገለጸች ከምትገኝው ኢትዮጵያ ጋር የሚኖረው ውጥረት ወደ ከፍተኛ ሁኔታ ሊያድግ እንደሚችል ነው ያሳሰበው፡፡
በሶማሊያ ለሚገኙ የሰላም አስከባሪ ሀይሎች ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርገው የአውሮፓ ህብረት ከተመድ እና ከአፍሪካ ህብረት ጋር ባደረገው ውይይት በአዲሱ ልዑክ ውስጥ የግብጽን ተሳትፎ እንደማይቃወሙ መናገራቸውን የህብረቱ ቃል አቀባይ ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ማን በአዲሱ ልኡክ ውስጥ እንደማይሳተፍ እና እንደሚሳተፍ ህብረቱ የመምረጥ ሃላፊነት የለውም ያሉ ሲሆን ነገር ግን ሁሉም የልኡኩ አባላት መቶ በመቶ አልሸባብን መዋጋት ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጋቸውን እንከታተላለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አትሚስን በሚተካው ልዑክ ዙርያ ባሳለፍነው ሀሙስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ አካሄዶ ነበር፡፡
የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ባለፉት አስርተ አመታት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የተደረገውን ጥረት ወደ ኋላ እየመለሰው ነው ያለው ምክር ቤቱ ልዩነታቸውን በአፋጣኝ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡