ዛምቢያ የጸረ ሙስና ተቋሟ በሙስና ተዘፍቋል በሚል አመራሮቹን ከስራ አገደች
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሙስናን እንዲከላከሉ የተሾሙ የጸረ ሙስና ቦርድ አባላትን ከስራ አግደዋል
የጸረ ሙስና ቦርድ አባላቱ በሙሰኞች ላይ የተጀመሩ ምርመራዎችን ጉቦ እየተቀበሉ አቋርጠዋል ተብሏል
የዛምቢያ ጸረ ሙስና ቦርድ አባላት በሙስና ተጠርጥረው ከስራ ታገዱ፡፡
ደቡብ አፍሪካዊቷ ሀገር ዛምቢያ ሙስና ከተንሰራፋባቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን በስልጣን ላይ ያሉት የወቅቱ ፕሬዝዳንት ሀኪንዴ ሂቺለማ በሙስና ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስዱ በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማሉ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከሶስት ዓመት በፊት ወደ ስልጣን እንደመጡም በቀድሞው የሀገሪቱ መንግስት አስታዳድር ወቅት በሙስና ተግባር የተሳተፉ አመራሮች ላይ ጥብቅ ምርመራ እንዲደረግ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በሚል አዲስ የጸረ ሙስና ቦርድ አቋቁመው ነበር፡፡
ይሁንና ሙስናን እንዲታገል የተቋቋመው ይህ ተቋም ራሱ በሙስና ተዘፍቆ ተገኝቷል በሚል የጸረ ሙስና ቦርዱ እንዲፈርስ መደረጉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ላለፉት 8 ወራት ደመወዝ ሳይቀበሉ እየሰሩ መሆኑ ተገለፀ
እንደ ዘገባው ከሆነ የዛምቢያ ጸረ ሙስና ቦርድ አራት ከፍተኛ አመራሮች ያሉት ሲሆን ቦርዱ በሙስና ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው የነበሩ ሰዎችን ጉቦ እየተቀበሉ ምርመራውን እንዲቋረጥ አድርገዋል፡፡
በተለይም በቦርዱ ውስጥ ይሰራ የነበረ አንድ ባለሙያ በሙስና ተጠርጥረው ምርምራ ሲደረግባቸው የነበሩ የቀድሞ ፖለቲከኞች እጅ መንሻ እየሰጡ ምርመራቸው እንደ ተቋረጠላቸው ይፋ አድርጓል፡፡
ይህን ተከትሎ ጉዳዩ በመላው ዛምቢያ ዋነኛ የወቅቱ መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን የጸረ ሙስና ቦርድ አመራሮች አስቀድመው ራሳቸውን ከሃላፊነት በማግለል ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ዘግይቶ ባወጣው መግለጫ የጸረ ሙስና ቦርድ አመራሮች ራሳቸው በሙስና በመዘፈቃቸው ምክንያት ቦርዱ እንዲፈርስ መወሰኑን አስታውቋል፡፡