ዛምቢያ የአሜሪካ ዶላር ጥቅም ላይ እንዳይውል ልትከለክል ነው
በአዲሱ መመሪያ መሰረት በሀገር ውስጥ ግብይት ዶላርን ጨምሮ የውጭ ገንዘቦችን መጠቀም 10 አመት የሚያስቀጣ ወንጀል ይሆናል
ከ2010 እስከ 2020 የሀገሪቱ እዳ ከ16 በመቶ ወደ 140 በመቶ አሻቅቧል
ዛምቢያ የአሜሪካ ዶላር ጥቅም ላይ እንዳይውል ልትከለክል ነው
የዛምቢያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ገንዘቦች በተለይም የአሜሪካ ዶላር በሀገር ውስጥ ግብይት ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚከለክል ረቂቅ ህግ አውጥቷል።
ህጉ ተግባራዊ ከሆነ ሲሆን ሁሉም የሀገር ውስጥ የመንግስት እና የግል ግብይቶች በዛምቢያ መገበያያ ገንዘብ "ክዋቻ" ብቻ እንዲደረግ ያስገድዳል።
ባንኩ በዶላር የሚደረጉ የሀገር ውስጥ ግብይቶች እየጨመረ መሄድ እንዳሳሰበው ሲገልጽ ነበር።
የዛምቢያ ባንክ የለቀቀው ረቂቅ ህግ እንደሚያሳየው ከሆነ ዶላርን ጨምሮ ሌሎች የውጭ ሀገራት ገንዘቦችን በሀገር ውስጥ ግብይት መጠቀም በ10 አመት ጽኑ እስራት ወይም ተመጣጣኝ በሆነ ገንዘብ ያስቀጣል።
በከፍተኛ ኢኮኖሚያው ጫና ውስጥ የምትገኝው ሀገሪቱ ከ2010 እስከ 2020 ጥቅል ሀገራዊ ምርቷ ከ29 ቢሊየን ዶላር ወደ 19 ቢሊየን ዶላር ያሽቆለቆለ ሲሆን በአንጻሩ የውጭ እዳዋ ከ16 በመቶ ወደ 140 በመቶ አሻቅቧል፡፡
በ2023 መጨረሻ ወራት 11 በመቶ የዋጋ ንረት የተመዘገበባት ዛምቢያ በሀገሪቱ የሚገኝው ህገ ወጥ የማአድን ንግድ የውጭ ሀገራት ገንዘብ በገበያ ውስጥ እንዲሰራጭ ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
60 በመቶ ህዝቧ ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ሲሆን የድህነት ምጣኔው ከከተማ ይልቅ በገጠሩ ይከፋል፡፡
ስራ አጥነትን በተመለከተ 31.9 በመቶ የስራ አጥ ምጣኔ ያላት ሲሆን እነኚህን ኢኮኖሚያው ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የተለያዩ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
በገበያ ውስጥ የውጭ ሀገራት ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ መሰራጨት የዛምቢያ መገበያያ ገንዘብ “ካዋቻን” የመግዛት አቅም በእጅጉ እንደቀነሰው እንዲሁም የምንዛሪ ገበያውንም ማቃወሱ ተሰምቷል፡፡
የሀገሪቱ የገንዘብ ሚንሰቴር ባወጣው መግለጫ በውጭ ሀገራት ገንዘብ የሚፈጸም ግብይት መጨመር ሸቀጦችን ለመገበያየት እና ለአገልግሎት ክፍያ የሀገሪቱ ገንዘብ ተቀባይነትን አሳጥቷል ነው ያለው፡፡
በ2012 ዛማቢያ ተመሳሳይ ህግ ገቢራዊ አድርጋ የነበረ ሲሆን ከሁለት አመታት በኋላ ህጉ ተሸሮ ዶላር በሀገር ውስጥ ገበያ ጥቅም እንዲሰጥ ፈቅዳ ሰጥታ ነበር፡፡
በማዕድን ኤክስፖርት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ የምትመራው ዛምቢያ ከ2023 ጀምሮ የበረታው የኮሌራ ስርጭት እንዲሁም ድርቅ በግብርና ምርቷ እና በአጠቃላይ ኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡
በከፍተኛ የውጭ እዳ ጫና ውስጥ የምትገኝው ሀገር የውጭ ሀገራት ገንዘብ ተጨማሪ ምጣኔ ሀብታዊ ጫናን ማስከተሉን ተከትሎ በሀገር ውስጥ ገብይት የውጭ ሀገራትን ገንዘብ መጠቀም በጥብቅ እንዲከለከል አድርጋለች፡፡