የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ላለፉት 8 ወራት ደመወዝ ሳይቀበሉ እየሰሩ መሆኑ ተገለፀ
ፕሬዝዳንት ሀድንኬ ሂቺሌማ ወደ ስልጣን የመጣሁት ደመወዝ ፈልጌ አይደለም ብለዋል
ሂቺሌማም የተከበሩ የሚሉና ሌሎች የማዕረግ ስሞችን እንደማይፈልጉ አስታውቀዋል
የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ሀድንኬ ሂቺሌማ ላለፉት ስምንት ወራት ምንም ደመወዝ ሳይቀበሉ እየሰሩ መሆኑን የሀገሪቱ የፋይናነስ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የዛምቢያ የፋይናነስ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ ፕሬዝዳንት ሀድንኬ ሂቺሌማ “ህዝብን ለማገልገል ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ደመወዛቸውን በራሳቸው ፍቃድ አልወሰዱም”።
ፕሬዝዳንት ሀድንኬ ሂቺሌማ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ የሀገሪቱን ከፍተኛ ስልጣን ለመያዝ ያነሳሳቸው ደመወዝ እንዳልሆነ አስታውቀዋል።
“የደመወዝ ጉዳይ ምንም አይደለም፤ ምክንያቱም ወደ ቢሮ እንደንገባ ያነሳሳን ህዝብን ማገልገል እንጂ ገንዘብ አይደለም፤ ደመወዝ ያለተቀበልኩት መንግስት ከልክሎኝ ሳይሆን በራሴ ፍቃድ ነው” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሀድንኬ ሂቺሌማ አክለውም የተከበሩ የሚሉ እና ሌሎች በሺዎች በሚቆጠሩ የማዕረግ ስሞች መጠራት እንደማይፈልጉ ያስታወቁ ሲሆን፤ ሚስተር ፐሬዝዳንት የሚለው መጠሪያ በቂያቸው እንደሆነም አስታውቀዋል።
የ59 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ሀድንኬ ሂቺሌማ ኢኮኖሚስት እንዲሁም በርካታ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ትስስር ያላቸው የንግድ ሰው ሲሆኑ፤ ከ15 ዓመታት የተቃዋሚ ፓርቲ ቆይታ በኋላ ኤድጋር ሉንጉን በመሸነፍ የዛምቢያ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል።
ሀድንኬ ሂቺሌማ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ሙስናን ከስር መሰረቱ በማስወገድ እና ለብዙሃኑ በተለይም ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም የታመመውን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ለመፈወስ ቃል ገብተው እንደነበረም ይታወሳል።