በዛምቢያ ለግርዛት የተጠለፉ 48 ታዳጊዎችን ማስለቀቅ መቻሉ ተነገረ
በሀገሪቱ እድሜያቸው ከ10 እስከ 17 ዓመት የሆናቸው ታዳጊ ወንዶች ወደ ካምፕ ተወስደው የሚገረዙበት ስርአት “ሙካንዳ” ይሰኛል
ታዳጊዎችን ያለቤተሰቦቻቸው ፈቃድ የሚወስዱ አካላት እስከ ስድስት ወራት በጫካ ውስጥ በማቆየት ባህላዊ ግርዛቱን ይፈጽማሉ ተብሏል
በዛምቢያ ለግርዛት ተጠልፈው የተወሰዱ 48 ታዳጊዎችን መታደግ መቻሉ ተነገረ።
የታዳጊዎቹ ወላጆች ለፖሊስ ሪፖርት በማቅረባቸው በተካሄደ አሰሳ በባህላዊ መንገድ ግርዛት ከሚፈጸምበት ካምፕ ልጆቹን ማስወጣት ተችሏል ነው የተባለው።
ከሊቪንግስተን ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ በተቋቋመው ህገወጥ ካምፕ ውስጥ ከተገኙት ታዳጊዎች ውስጥ ሶስቱ በምላጭ በመገረዛቸው በተፈጠረ ችግር ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል ብለዋል የሀገሪቱ ባለስልጣናት።
አንድ ታዳጊም ለሁለት ሳምንት ያህል የኤችአይቪ መድሃኒቱን መውሰድ እንዳልቻለ ባለስልጣናትን ጠቅሶ የዛምቢያ ብሮድካስቲን ኮርፖሬሽን ዘግቧል።
በዛምቢያ እድሜያቸው ከ10 እስከ 17 የሚደርስ ታዳጊዎች ሚስጢራዊና ባህላዊ የግርዛት ስነስርአት ይደረላቸል።
“ሙካንዳ” የሚሰኘው ይህ ወደ ወንድነት መሸጋገሪያ ስርአት እንዲፈጸም በተለያዩ አካባቢዎች ካምፖችን የሚያቋቁሙ አካላት የታዳጊዎቹን ወላጆች ይሁንታ ሳያገኙ ጭምር ነው ወደ ጫካ የሚወስዷቸው።
አንዳንዶቹ በፈቃደኝነት የሚጓዙ ቢሆንም ባልተመቸና በባህላዊ መንገድ የሚካሄደውን ግርዛት የሚቃወሙ በርካቶችም ታፍነው ከመወሰድ አይድኑም።
የግርዛት ካምፖቹን የሚከፍቱትና ለባህልና ወጋችን ተቆርቋሪ ነን የሚሉ አካላት ያልተገረዙ ወንድ ታዳጊዎችን የሚያስሱት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሲሆን፥ ከልካይ እንደሌላቸውም ነው የሚነገረው።
በዛምቢያ የስርአተ ጾታ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራር የሆኑት ማይንጋ ካቢካ በህገወጥ ካምፖች “ሙካንዳ” ስርአት የሚፈጽሙ አካላትን ያስጠነቀቁ ሲሆን፥ 48ቱ ታዳጊዎች የተገኙበት ካምፕም እንዲቃጠል ማድረጋቸው ተገልጿል።
“ባህልና ወጋችን መጠበቅ ብንፈልግም ስርአት ግን መከበር አለበት፤ ከህግ አግባብ ውጭ እንዲህ አይነት ተግባር መፈጸም አትችሉም” ሲሉም ድርጊቱን ለሚፈጽሙ አካላት የማስጠንቀቂያ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዛምቢያ ዴይሊ ሜል ጋዜጣ በበኩሉ ታዳጊዎቹን ለግርዛት እስከ ስድስት ወራት በካምፕ ውስጥ የሚያቆዩት አካላት ባህላዊ ልማድን የማስቀጠል አላማ አለን ቢሉም ክፍያ ሲጠይቁ እንደነበር ዘግቧል።
አንዳንድ ወላጆችም ልጆጃቸው በካምፖች ውስጥ እንዲገረዙ ባይፈቅዱም በስልክ እየተደወለ እስከ 75 ዶላር ክፍያ እንዲፈጽሙ መጠየቃቸውን ነው ዘገባው የጠቆመው።
በዛምቢያ የወንዶች ግርዛት በጤና ማዕከላት የሚሰጥ ቢሆንም የተወሰኑ የጎሳ አባላት ባህላዊውን መንገድ ይመርጣሉ ተብሏል።