የአውሮፓ ሀገራት 40 በመቶ የጋዝ ፍላጎታቸውን ከሩሲያ በሚያገኙት ነው የሚያሟሉት
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሩሲያ በኖርድ ስትሪም የጋዝ ማስተላለፊያ ላይ የነዳጅ ጦርነት እየተከፈተች ነው ሲሉ ከሰሱ።
ፕሬዝዳንቱ ነዳጅ ወደ አውሮፓ በሚገባበት የኖርድ ስትሪም መስመር ላይ ነዳጅ እንዳይገባ በማቋረጥ ሕዝብን እያሸበረች እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ኖርድ ስትሪም በአውሮፓ የሚገኝ የነዳጅ ማስተላለፊያ ሲሆን ነዳጅ ወደ አውሮፓ የሚገባበት ማስተላለፊያ ነው። የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሩሲያ እክል እንደፈጠረች የከሰሱትም በዚሁ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ላይ እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል።
- “ያለ ሩሲያ ጋዝና ነዳጅ እንዴት መቀጠል ይቻላል” የሚለው የአውሮፓ ሀገራትን ማሳሰቡ ተገለፀ
- የአውሮፓ ህብረት የሩሲያ የተፈጥሮ ጋዝን ለመተካት አፍሪካን እያማተረ ነው
በባልቲክ ባህር ውስጥ የተዘረጋውና ነዳጅ ከሩሲያ ወደ ጀርመን የሚተላለፍበት ይህ መስመር እንዲዘጋና ነዳጅ ፈላጊ ሕዝብ እንዲሸበር አድርጋለች ሲሉም ዘለንስኪ ሞስኮን እየወቀሱ ነው።
ሩሲያ አሁን ላይ ወደ አውሮፓ የሚገባ የነዳጅ አቅርቦትን እየቀነሰችና እያቋረጥ እንደሆነም ነው የዩክሬኑ መሪ ያነሱት።
አሁን ላይ በኖርድ ስትሪም በኩል ከሩሲያ ወደ ጀርመን የሚመጣው ጋዝ ቀደም ሲል ከነበረው የቀነሰ መሆኑ ተገልጿል። ይህ ድርጊትም ወንጀል መሆኑን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ተናግረዋል።
ከወር በፊት የአውሮፓ ግዙፉ ጋዝ ማስተላለፊያ ለጥገና በሚል ከጥቅም ውጭ ሆኖ የነበረ ሲሆን በወቅቱ በአውሮፓ ከፍተኛ ፍርሃት ነበር። ይሁንና የጋዝ ማስተላለፊያው መልሶ ወደ አገልግሎት በመግባቱ በአውሮፓ ያለው ስጋት እየቀነሰ መጥቷል።
ሩሲያ ከአሜሪካና አጋሮቿ የተጣለባትን ማዕቀብ ለማካካስ በሚል የሀገሯን ጋዝ በራሷ የመገበያያ ገንዘብ ለመሸጥ ውሳኔ ማሳለፏ ይታወሳል።
የአውሮፓ ህብረት ከሩሲያ ወደ አባል ሀገሮቹ የሚገባው የጋዝ መጠን እንዲቀንስ ተደጋጋሚ ማብራሪያ ቢሰጥም ሀገራቱ ግን ከሩሲያ ጋዝ ውጭ ፍላጎትን ማሳካት እንደማይቻል በመግለጽ ከሞስኮ ጋር እየነገዱ ነው።