ህብረቱ እስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስ 50 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ጋዝ ለመግዛት አቅዷል
የአውሮፓ ህብረት ከሩሲያ የሚገዛውን የተፈጥሮ ጋዝን ለመተካት ፊቱን ወደ አፍሪካ ማዞሩ ሪፖርት አመላከተ።
ከአውሮፓ ህብረት የተገኘ ረቂቅ ሰንድን ዋቢ አድርጎ በሉምበርግ ባወጣው ሪፖርት፤ በአፍሪካ ውስጥ ያሉ እንደ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል እና አንጎላ ያሉ ሀገራት በአብዛኛው ጥቅም ላይ ያልዋለ ከፍተኛ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አላቸው።
ህብረቱ በፈረንጆቹ እስከ 2030 ድረስ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባውን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ በ50 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ማሳደግ እቅድ እንዳለውም ተመላክቷል።
ለዚህም ህብረቱ ከሩሲያ በስተቀር ወደ ሌሎች ሀገራት የጋዝ ቧንቧ መስመር ጨምሮ በተለያዩ የጭነት አማራጮች የሚያስገባውን የጋዝ መጠን ለመጨመር ማቀዱም ተገልጿል።
የአውሮፓ ህብረት እቅዱን ለማሳካት ከአሜሪካ ጋር ያለውን የፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ስምምነትን ሙሉ በሙሉ መተግበር እንዳለበትም ተነግሯል።
እንደሁም እንደ ግብፅ፣ እስራኤል፣ አዘርባጃን እና አውስትራሊያ ካሉ አቅራቢዎች ጋር ያለውን የንግድ ስምምነት ማጠናከር እንደሚጠበቅበትም ተመላክቷል።
ሩሲያ ከመጋቢት መጨረሻ ቀናት ጀምሮ አውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ወዳጅ ላልሆኑ ለሌሎች ሀገራት ነዳጅ በሩብል እንዲሸጥ መወሰኗ ይታወሳል።
የአውሮፓ ህብረት የሩሲያን አዲስ የነዳጅ ግዥ ውሳኔ ውድቅ ያደረገ ቢሆንም የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በበኩሉ ማዕቀቡን ሳይጥሱ የአውሮፓ የነዳጅ ኩባንያዎች ከሩሲያ በሩብል እንዲገዙ ፈቅዷል።
ከ10 በላይ የአውሮፓ ሀገራት ነዳጅ በሩብል ከሩሲያ በመግዛት ላይ ሲሆኑ ፖላንድ እና ቡልጋሪያ ነዳጅ ለመግዛት ሩብል ባለማቅረባቸው ምክንያት ሩሲያ ነዳጅ መሸጥ ማቆሟ አይዘነጋም።
ቻይና ባሳለፍነው ተመሳሳይ ወራት ከሩሲያ የገዛችው የነዳጅ መጠን ከዘንድሮው ጋር ሲነጻጸር በ60 በመቶ ማደጉን በትናትናው እለት የወጣ ሪፖት ያመላክታል።