ዘለንስኪ አሜሪካ የምትወስዳቸው ወሳኝ እርምጃዎች ጦርነቱ እንዲያበቃ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተናገሩ
ዘለንስኪ አሁን በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ለመሳተፍ በአሜሪካ ይገኛሉ
ዘለንስኪ ሩሲያን ለማሸነፍ ይረዳል ያሉትን የድል እቅድ ለማሳየት እና በአሜሪካ የዩክሬን ፖሊሲ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ወደ ዋሽንግተን ይጓዛሉ
ዘለንስኪ አሜሪካ የምትወስዳቸው ወሳኝ እርምጃዎች ጦርነቱ እንዲያበቃ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተናገሩ።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ አሜሪካ የምትወስዳቸው ወሳኝ እርምጃዎች ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ጦርነትን በቀጣይ አመት ማብቃት ሊያፋጥነው ይችላል ብለዋል።
"አሁን፣ በአመቱ መጨረሻ በዩክሬን እና በአሜሪካ መካከል ያለውን ግንኘነት ለማጠናከር ትክክለኛ አጋጣሚ አለን" ሲሉ ዘለንስኪ ከአሜሪካ ባይፓርታዚያን ኮንግረስ ልኡክ ጋር ከተወያዩ በኋላ በቴሌግራም ገጻቸው አስፍረዋል።
"አሁን የሚወሰድ ወሳኝ እርምጃ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገው ወረራ እንዲያበቃ ያፋጥነዋል።"
ዘለንስኪ አሁን በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ለመሳተፍ በአሜሪካ ይገኛሉ። በዚህ ሳምንት መጨረሻ ሩሲያን ለማሸነፍ ይረዳል ያሉትን የድል እቅድ ለማሳየት እና በአሜሪካ የዩክሬን ፖሊሲ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ወደ ዋሽንግተን ይጓዛሉ።
ዘለንስኪ እቅዱን ለአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና እሳቸውን ይተካሉ ተብለዉ ለሚጠበቁት ካማላ ሀሪስ እና ዶናልድ ትራምፕ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል። እቅዱ በምዕራባዊውያን የሚደገፍ ከሆነ የስነልቦናን ጨምሮ በሞስኮ ላይ ሰፊ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር፣ ፑቲን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጦርነቱን እንዲያቆሙ ያስገድዳቸዋል ብለዋል ዘለንስኪ።
ዘለንስኪ ባለፈው አርብ እለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "የድል እቅዱ ስትራቴጂካዊ አጋሮቻችን የሚወስዱትን ፈጣን እና ተጨባጭ እርምጃዎችን የያዘ ነው።"
ዘለንስኪ አክለውም እቅዱ ዩክሬን በዚህ አመት መጨረሻ ለምታዘጋጀው እና ሩሲያን ለመጋበዝ ለምትፈልግበት ለሁለተኛ ዩክሬን መር የሰላም ጉባኤ እንደ ድልድይ ሆኖ ያገልግል ብለዋል።
ሁለቱ አካላት ንግግር ጦርነቱን ለማስቆም ያስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ የራራቀ ነው።
ዘለንስኪ ዩክሬን የኔቶ እና የአውሮፓ ህብረት አባል እንድትሆን እና ሩሲያ ከዩክሬን ግዛት ሙሉ በሙሉ እንድትወጣ ይፈልጋሉ። ነገርግን ፑቲን የሰላም ንግግር የሚጀምረው ኪቪ በምስራቅ እና በደቡብ ከሚገኙት ቦታዎች ለቃ ስትወጣ እና የኔቶ አባል የመሆን ጥያቄዋን ስትተው ብለዋል።
ዘለንስኪ ይህን ጉዞ ያደረጉት ዩክሬን አጣብቂኝ ውስጥ በገባችበት ወቅት ነው። ትራምፕ በመጭው ጥቅምት ወር መጨረሻ የሚካሄደውን ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ በዋናነት በአሜሪካ ወታደራዊ እና የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ጥገኛ በሆነቸው ዩክሬን ላይ የፖሊስ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ።
ትራምፕ በቴለቪዥን በተካሄደ የምርጫ ክርክር ወቅት ዩክሬን ሩሲያን እንድታሸንፍ ይፈልጉ እንደሆነ ተጠይቀው ለመመለስ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ምርጫ የሚያሰንፉ ከሆነ ቢሮ ሳይገቡ ጦርነቱን ለማስቆም እንደሚሞክሩ ትራምፕ ተናግረዋል።
ትራምፕ በትናንትናው እለት ዘለንስኪ ዲሞክራቶች ምርጫውን እንዲያሸንፉ ይፈልጋሉ ሲሉ ተናግረዋል። ዘለንስኪ ግን ከዚህ በፊት ኃይት ሀውስን ከሚቆጣጠር ከማንኛውም አካል ጋር እንደሚሰሩ መግለጻቸው ይታወሳል።
የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ባይደን የዘለንስኪን ጦርነቱን ለማሸነፍ ያስችላል የተባለውን እቅድ ለማየት መጓጓታቸውን ተናግረዋል።
ዘለንስኪ ይህ እቅድ የሚሳካው በባይደን ውሳኔ ነው ብለዋል።