15ኛ ወሩን የያዘው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ያስከተለው ጉዳትንበተመለከተ የሚወጡ መረጃዎች አወዛጋቢ ናቸው
ከሟቾቹ ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት (10 ሺህ) የዋግነር ቅጥረኛ ወታደሮች ናቸው ተብሏል።
የአሜሪካ የብሄራዊ ደህንነት ቃል አቀባዩ ጆን ኪርቢ በሰጡት መግለጫ፥ ከ80 ሺህ በላይ ሩሲያውያን መቁሰላቸውንም ተናግረዋል።
ሞስኮ በባክሙት በኩል ወደ ምስራቃዊ ዩክሬን (ዶንባስ) ለመስፋፋት እያደረገች ያለው ሙከራ ብዙ ዋጋ እንዳስከፈላት ጆን ኪርቢ አንስተዋል።
"ሩሲያ አንድም ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ያለው ይዞታ መቆጣጠር አልቻለችም" ሲሉም ነው ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ ሩሲያ አብዛኛውን ባክሙት መቆጣጠሯ የዶኔስክ አካባቢን ሙሉ በሙሉ በእጇ ለማስገባት እንደሚያስችላት ነው ተንታኞች የሚያነሱት።
ከተማዋ ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ባይኖራት ከባለፈው አመት ጀምሮ ሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ ዋጋ ባልከፈሉ ነበርም ይላሉ።
ጆን ኪርቢ ሚስጢራዊ ሰነዶችን ዋቢ አድርገው ሩሲያ የገጠማትን ጉዳት ሲጠቅሱ በዩክሬን በኩል የደረሰውን አላብራሩም።
ለዚህም ምክንያታቸውን ሲገልፁ "ዩክሬናውያን ተጎጂዎች፣ ሩሲያ ደግሞ ወራሪ ስለሆኑ ነው" በማለት የአጥቂውን ጉዳት ብቻ መጥቀስ ተገቢ ስለመሆኑ ነው የጠቆሙት።
ቢቢሲ በአሜሪካ የተጠቀሰውን አሃዝ ማረጋገጥ አልቻልኩም፤ ሩሲያም ምንም አልሰጠችም ብሏል።