የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በ2025 እንዲጠናቀቅ እፈልጋለሁ - ዜለንስኪ
የትራምፕ ዳግም መመረጥ በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ በምዕራቡ አለም ከፍተኛ የፖሊሲ ለውጥን እንደሚያስከትል እየተነገረ ነው
የቡድን 7 አባል ሀገራት ለኬቭ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልደሚር ዜለንስኪ ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ ጦርነቱ በሚቀጥለው አመት እንደሚጠናቀቅ ተስፋ እንዳለቸው ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንቱ በዛሬው እለት ከዩክሬን ሬዲዮ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ግጭቱ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
“ሆኖም የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ፍላጎት የላቸውም” ያሉት ዘለንስኪ፤ ሞስኮ ውግያውን በቀጠለችበት ሁኔታ ስለ ሰላም መነጋገር አዳጋች ሊያደርገው ይችላል" ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም "በእኛ በኩል ይህን ጦርነት በሚቀጥለው አመት እንዲያበቃ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን ቀዳማዊ አማራጭ ለማድረግ ዝግጁ ነን" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ የሩሲያ ወታደሮች በየካቲት 2022 በተጀመረው ዘመቻ ከያዟቸው ሁሉም አካባቢዎች ለቀው እስካልወጡ ድረስ ከሞስኮ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲናገሩ መቆየታቸው ይታወሳል።
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን መምጣት በዩክሬን ጦርነት ላይ በምዕራቡ አለም ከፍተኛ የፖሊሲ ለውጥን እንደሚያስከትል እየተነገረ መሆኑን ዶቼ ቬለ ዘግቧል፡፡
በኬቭ እና በሞስኮ መካከል ያለው ዲፕሎማሲ ግንኙነት በሁሉም ደረጃ ቆሟል፤ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን ጋር የሚደረገውን ውይይት የሚቀበሉት ዩክሬን ሞስኮ የያዘችው የዩክሬን ግዛቶች ላይ ጥያቄ የማታነሳ ከሆነ ብቻ ነው ይላሉ፤ ዜለንስኪ በበኩላቸው ይህን ሀሳብ ውድቅ ያደርጋሉ፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን ከጀርመኑ መራሄ መንግስት ጋር በትላንትናው እለት በነበራቸው የስልክ ውይይትም በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆም የትኛውም ስምምነት የሩሲያን የደህንነት ጥያቄዎች እና አዲስ የግዛት እውነታዎችን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚኖርበት ስለመናገራቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቡድን 7 ለዩክሬን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
የቡድኑ አባል ሀገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ ዩክሬን ለሉዓላዊነት፣ ለነጻነት፣ ለግዛታዊ አንድነት የምታደርገውን ትግል በመደገፍ በጋራ መቆማቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
በተጨማሪም “ሩስያ የአለም አቀፍ ሰላም እና ደህንነትን አደጋ ላይ ከሚጥል ድርጊት እንድትቆጠብ” በድጋሚ አስጠንቅቀዋል፡፡
ጦርነቱ ከዩክሬን እና ከሩሲያ ወደ ውጭ በሚላኩ እህል ምርቶች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ በማሳደሩ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች የምግብ ዋስትና ላይ ትልቅ ችግር ፈጥሯል ያለው መግለጫው፤
ዩክሬናውያን መሬታቸውን፣ ባህላቸውን እና ህዝባቸውን በመጠበቅ ረገድ ወደርየለሽ ጽናት እና ቁርጠኝነት" አሳይተዋል ብለዋል።
ቡድን 7 አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ብሪታንያ የሚያካትት ሲሆን ጣሊያን በአሁኑ ወቅት የቡድኑን ተለዋጭ የፕሬዝዳንትነት ቦታ ይዛለች።