የአውሮፓ ህብረት በሩስያ ላይ የያዘውን የማዕቀብ ፖሊሲ እንዲያቆም የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚንስትር ጠየቁ
የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካ እና አጋሮቿ ከዩክሬን ጦርነት መጀመር በኋላ በሩስያ ላይ 16500 የተለያዩ ማዕቀቦችን ጥለዋል
የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚንስትር ማዕቀቦቹ የአውሮፓን ኢኮኖሚ እየጎዱ ነው ብለዋል
የአውሮፓ ህብረት በሩስያ ላይ የያዘውን የማዕቀብ ፖሊሲ እንዲቀይር የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚንስትር ቪክተር ኦርባን ጠየቁ፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ በሞስኮ ላይ እየተጣለ የሚገኝው ማዕቀብ የአህጉሩን ኢኮኖሚ ለውድቀት የሚዳርግ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
በ 2022 የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የአውሮፓ ህብረት የኢነርጂ ሴክተርን፣ ባንኮችን፣ የዓለማችን ትልቁ የአልማዝ ማዕድን አምራች ኩባንያ እና ሌሎች የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ያነጣጠረ በርካታ ማዕቀቦችን በሞስኮ ላይ ጥሏል።
ከህብረቱ አባል ሀገራት መካከል ከክሬምሊን ጋር ሞቅ ያለ ወዳጅነት እንዳላቸው የሚነገርላቸው ኦርባን ከአብዛኞቹ የአውሮፓ መሪዎች ጋር በተጣረሰ መልኩ ማዕቀቡ ከሩሲያ የበለጠ የአውሮፓን ኢኮኖሚ እንደሚጎዳ ሲናገሩ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ በትላንትናው ዕለት ከሀገራቸው የሬድዮ ጣብያ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ የአውሮፓ ህብረት የማዕቀብ ፖሊሲውን መገምገም አለበት ምክንያቱም እንዲህ ያለው ማዕቀብ ነዳጅን ጨምሮ ወሳኝ በሆኑ ሸቀጦች አለም አቀፍ ዋጋ ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዲታይ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ሃንጋሪ በአሁኑ ጊዜ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአውሮፓ ህብረት ሊቀመንበርነትን ይዛለች የአውሮፓ ህብረት መሪዎች በበኩላቸው በሞስኮ ላይ አዲስ ዙር ማዕቀብ ለመጣል እቅድ እያወጡ ነው።
ባሳለፍነው ሀሙስ ሻዶ ፍሊት በመባል የሚታወቁት የሩስያን ነዳጅ ወደ ውጭ ገበያ በድብቅ በሚያቀርቡ መርከቦች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ የህብረቱ የህግ አውጭ ቡድን አሳስቧል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ፣ አሜሪካ ብሪታንያ አውስትራሊያ ካናዳ እና ጃፓን ከዩክሬን ጦርነት መጀመር በኋላ በሩስያ ላይ 16500 የተለያዩ ማዕቀቦችን ጥለዋል፡፡
ማዕቀቦቹ በዋናነት በኢኮኖሚ ላይ ያነጣጠሩ ሲሆን የሀገሪቱ የገንዘብ እንቅስቃሴን ከማገድ ጀምሮ የሩስያን ባንዲራ የሰቀሉ የንግድ መርከቦች በወደቦቻቸው ላይ እንዳያርፉ እስከመከልከል ይደርሳል፡፡
በተጨማሪም የሞስኮ ባለጠጎች እና ከሀገሪቱ ጋር የንግድ ግንኙነት ያላቸው አለም አቀፍ የቴክኖሎጂ እና የንግድ ኩባንያዎችም የዚሁ ማዕቀብ ሰላባ ሆነዋል፡፡
ወርቅ እና ዳይመንድን የመሳሰሉ ሞስኮ በሰፊው የምታመርታቸው ማዕድናት እና ሸቀጦች በአውሮፓ ገበያ እንዳይቀርቡም ታግደዋል፡፡