በአለማችን ከ8 ሰዎች አንዱ ከልክ ላለፈ ውፍረት ተጋልጧል - ጥናት
የአለም ጤና ድርጅት የሃብታም ችግር ይመስል የነበረው ከልክ ያለፈ ውፍረት የድሃ ሀገራት ዜጎችንም ክፉኛ እየፈተነ ነው ብሏል
ላልተመጣጠነ ውፍረት የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር በ1990 ከነበረበት በአራት እጥፍ መጨመሩም ተገልጿል
በአለማችን ከ1 ቢሊየን በላይ ሰዎች ከልክ ላለፈ ውፍረት ተጋልጠዋል አለ የአለም ጤና ድርጅት።
ድርጅቱ ከላንሴት ጋር በመተባበር ባደረገው ጥናት “ወረርሽኝ” ያለው ችግር ከወጣቶች በበለጠ በህጻናትና ታዳጊዎች ላይ እየተስፋፋ መሄዱንም አመላክቷል።
በፈረንጆቹ 1990 ከቁመት እና እድሜያቸው ጋር የማይመጣጠን ውፍረት ውስጥ የነበሩ ሰዎች ቁጥር 226 ሚሊየን ነበር። በ2022 ይህ አሃዝ በአራት እጥፍ አድጎ ወደ 1 ቢሊየን 380 ሺህ ከፍ ብሏል።
ላንሴት በ190 ሀገራት የሚገኙ 220 ሚሊየን ሰዎች ቁመት እና ክብደትን በመለካት የተካሄደው ጥናት ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ከልክ ላለፈ ውፍረት ተጋላጭ መሆናቸውን አሳይቷል ብሏል።
በ2022 ከልክ ላለፈ ውፍረት የተጋለጡ ሴቶች ቁጥር 504 ሚሊየን መድረሱ ተገምቷልም ነው ያለው።
በ1990 31 ሚሊየን አካባቢ የነበረው የችግሩ ተጠቂ ህጻናት ቁጥርም በ2022 ወደ 159 ሚሊየን ማደጉን የአለም ጤና ድርጅት እና ላንሴት ጥናት ያሳያል።
ጥናቱ በበርካቶች የሃብት ወይም የምቾት መገለጫ ተደርጎ ይወሰድ የነበረው ውፍረት የድሃ ሀገራትን ህጻናት እና ታዳጊዎች መፈተን ከጀመረ ዋል አደር ማለቱንም ፍራንስ 24 አስነብቧል።
የካሪቢያን፣ መካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ሀገራትም በችግሩ በስፋት እየተጠቁ መሆኑንም በማከል።
በቀጠናዎቹ የሚገኙ ሀገራት ዜጎች ከአውሮፓውያን በበለጠ ከልክ ላለፈ ውፍረት በመጋለጥ ላይ መሆናቸውን የጠቀሰው ጥናቱ፥ ውፍረት አሁን የሃብታሞች ብቻ ሳይሆን የመላው አለም ችግር ነው ብሏል።
ከልክ ያለፈ ውፍረት ከልብ ህመም እስከ ስኳርና የተለያዩ የካንሰር አይነቶች ተጋላጭነትን በብዙው ይጨምራል።
አመጋገብን ማስተካከል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና በጊዜ ህክምና ማግኘት ይገባል የሚለው የአለም ጤና ድርጅት፥ ክብደትን የሚጨምሩ ምግቦችና መጠጦች ላይ የሚጣለው ግብር እንዲጨምር ያበረታታል።